ችግኞችን ከመትከል ባለፈ ተንከባክቦ ማሳደግ እንደሚገባ ተገለፀ፡፡

ችግኞችን ከመትከል ባለፈ ተንከባክቦ ማሳደግ እንደሚገባ ተገለፀ፡፡

የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ

ችግኞችን ከመትከል ባለፈ ተንከባክቦ ማሳደግ እንደሚገባ ተገለፀ፡፡

የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ሰራተኞችና ኃላፊዎች በፍጥነት መንገዱ አካፋይ እንዲሁም ግራና ቀኝ በሚገኙ ቦታዎች ላይ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም አካሄዱ፡፡ ‹‹አንድ ችግኝ ለህዳሴ ግድብ›› በሚል መሪ ቃል በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደው ፕሮግራም አንድ አካል የሆነው የችግኝ ተከላ በ12/11/2010 ዓ.ም ተካሂዶ ውሏል፡፡

ኢንተርፕራይዙ በሀገሪቱ ያለውን የደን ሽፋን ከፍ ለማድረግ ታሳቢ ያደረገውን እንቅስቃሴ ለመደገፍ እንዲሁም እንደ ተቋም ኃላፊነትን ለመወጣት፤ ተሽከርካሪዎች የሚለቁት በካይ ጋዝ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የሚያመጣውን ተፅዕኖ ለመቀነስ፤ የመንገዱን ውበት በመጨመር ለዐይን ማራኪ አካባቢን ለመፍጠር፤ በመንገዱ አካፋይ ቦታ ላይ የተተከሉ ተክሎች በምሽት ከተቃራኒ አቅጣጫ የሚለቀቀውን የተሽከርካሪ ብርሃን ለመቀነስ ታስቦ ከ15,000 በላይ ችግኞች መትከል ተችሏል፡፡

ተቋሙ አገልግሎት መስጠት ከጀመረበት መስከረም 2007 ዓ.ም ጀምሮ የአረንጓዴ ልማትን በመደገፍ ችግኞችን የመትከልና የመንከባከብ ስራ እየሰራ ነው፡፡ የዘንድሮ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ከሌላው ጊዜ ለየት የሚያደርገው ኢንተርፕራይዙ በውስጥ አቅም የችግኝ ማፍያ ጣቢያ በማቋቋም ሁሉንም ችግኞች በማፍላት ማዘጋጀቱ ነው፡፡ ይህም በየዓመቱ ለችግኝ ግዥ አገልግሎት ይውል የነበረውን በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ወጪ ማስቀረት ችሏል፡፡

ከዚህም ጎን ለጎን ችግኞችን ከመትከል ባለፈ ተንከባክቦ በማሳደግ የሚፈለገው ለውጥ እንዲመጣ ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንደሚገባ የአካባቢ ጥበቃ ቡድን መሪ የሆኑት አቶ አብደላ መሀመድ ገልፀዋል፡፡

ኢንተፕራይዙም ለዚህ ምሳሌ መሆን እንደሚችል በመግለፅ በሐምሌ 2009 ዓ.ም የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፕሬዝዳንት ክቡር ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ በተገኙበት የችግኝ ተከላ መካሄዱን አስታውሰው በወቅቱ ከተተከሉት 19,550 ችግኞች ውስጥ 81% የሚሆኑት መፅደቃቸውን ተናግረዋል ፡፡ ለውጤቱም በየጊዜው ውሃ የማጠጣት፣ የመኮትኮትና የመንከባከብ ስራ መሰራቱ መሆኑን በማንሳት በርካታ ተቋማትም ከዚህ ልምድ መውሰድ እንደሚገባቸው ጠቁመዋል፡፡

 

ደህንነትዎ የክብር ስማችን ነው!