አገልግሎት

አገልግሎት

አገልግሎት

በኢትዮጵያ አሁን አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘውን የአዲስ አበባ- አዳማ እንዲሁም ወደ ፊት ግንባታቸው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት የሚጀምሩትን የክፍያ መንገዶች ለማስተዳደር የተቋቋመው የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ፤ አገልግሎት መስጠት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ለአፍታም ያልተቋረጠ የክፍያ መንገድ አገልግሎት እየሰጠ ነው፡፡ ደህንነቱ የተጠበቀ፤ ምቾቱ የተረጋገጠ፤ ዘመናዊነቱ የታየ፤ አስተማማኝነቱ የተመሰከረ እንዲሁም የጥራት ደረጃውን ያሟላ የክፍያ መንገድ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ አገልግሎቱ በስድስቱም የክፍያ ጣቢያዎች እየተሰጠ ነው፡፡ አገልግሎቱን ቀልጣፋ ለማድረግ በሁሉም የክፍያ ጣቢያዎች 19 የመግቢያና 29 የመውጫ በሮች ተዘጋጅተዋል፡፡ በሁሉም የክፍያ ጣቢያዎች “እንኳን ደህና መጡ” ብለው በመልካም ንግግር በሚቀበሉ እና “መልካም መንገድ” ብለው በሚሸኙ በመልካም ምኞት የተሞሉ ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች ታግዞ የእጅ በእጅ የክፍያ አገልግሎት ስርዓት በመጠቀም አገልግሎት ይሰጣል፡፡ በቀን በአማካይ ከ21 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎች እያስተናገደ የሚገኘው የክፍያ መንገድ ደንበኞች በመውጫ በር ላይ ሲደርሱ የአገልግሎት ክፍያ እንዲከፍሉ ይደረጋል፡፡ ለቀላል ተሽከርካሪ በኪ.ሜ 0.66፣ ለመካከለኛ ተሽከርካሪ 0.79 እንዲሁም ለከፍተኛ ተሽከርካሪ 0.92 ሳንቲም ነው፡፡ በተጨማሪም የ 1 ወር እና 3 ወር የቅድመ ክፍያ ካርድ በማዘጋጀት ደንበኞች እንዲገለገሉ ይሆናል፡፡ ደንበኞች ወይም ተቋማት በክፍያ መውጫ በሮች ላይ የሚያሳልፉትን ጊዜ ለመቀነስ፣ ከጥሬ ገንዘብ ጋር ያለን ግንኙነት ለማሳነስ እንዲሁም አገልግሎቱን በመጠቀም የሚገኘውን ቅናሽ ለማግኘት ያስችላል፡፡ አሽከርካሪዎች በመንገዱ የተቀመጠውን የፍጥነ ት መሰን ጠብቀው በማሽከርከር በአገልግሎት መስጫ በመንገዱ ክልል ውስጥ ሲጠቀሙ ቀልጣፋ አገልግሎት ያገኛሉ፡፡ በመሆኑም በመግቢያ በሮች ላይ ለቀላል ተሽከርካሪዎች 15 ሰከንድ እና ለከባድ ተሽከርካሪዎች 20 ሰከንድ እንዲሁም በመውጫ በሮች ላይ ለቀላል ተሽከርካሪዎች 30 ሰከንድ እና ለከባድ ተሽከርካሪዎች 45 ሰከንድ ውስጥ አገልግሎት እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ አሽከርካሪዎች የሚሰጠውን ቀልጣፋና ፈጣን አገልግሎት ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ በመውጫ በር ላይ ሲደርሱ ትኬታቸውን በአቅራቢያ ቢያስቀምጡ፣ ዝርዝርብር ቢጠቀሙ ሊባክን የሚችለውን ጊዜ በማስቀረት የድርሻቸውን መወጣት ይችላሉ፡፡ ኢንተርፕራይዙ በዋናነት ከሚሰጠው የክፍያ መንገድ አገልግሎት በተጨማሪ የማስታወቂያ ቦታዎች ኪራይ፣ ተሽከርካሪዎችን በክሬን የማንሳትና የመጐተት፣ የተሽከርካሪ ማቆያ፣ የመንገድ ቁጥጥር (patrolling) እና የአምቡላንስ የመጀመሪያ ደረጃ ህክምና እርዳታ አገልግሎት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የማስታወቂያ ቦታዎች ኪራይ ስራ ዘርፍ በስፋት በመንገዱ በሚገኙ የመሸጋገሪያ ድልድዮች ላይ ምርትና አገልግሎታቸውን ማስተዋወቅ ለሚፈልጉ ድርጅቶች የማስታወቂያ ቦታዎች ኪራይ አገልግሎት መስጠት ነው፡፡ የክፍያ መንገዱ በቀን ከ21 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎች ማስተናገዱ እና ለ24 ሰዓት ያልተቋረጠ አገልግሎት መስጠቱ እንዲሁም በብዙ ተመልካቾች እይታ ውስጥ መዋሉ በተጠቃሚዎች ዘንድ ተመራጭ ከመሆኑም በላይ ተቋማት ምርትና አገልግሎትቸውን የሚያስተዋውቁበት አጋጣሚ ይፈጥራል፡፡ ተገልጋዮች መንገዱን በሚጠቀሙበት ወቅትበድንገተኛ አደጋ በቴክኒክ ብልሽት አልያም ልዩ ልዩ በሆኑ አጋጣሚዎች በተሽከርካሪዎቻቸው ላይ ችግር ሲገጥማቸው በክሬን የማንሳትና የመጐተት አገልግሎት እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ ከዚህም ጐን ለጐን ተሽከርካሪዎቹ በጊዜያዊነት አስተማማኝ የተሽከርካሪ ማቆያ ቦታ እንዲቆዩ ይሆናል፡፡ የ24/7 አገልግሎት የሚሰጠው የአዲስ አበባ – አዳማ የክፍያ መንገድ ደህንነቱ የተረጋገጠና አስተማማኝነቱን ጠብቆ እንዲሄድ የመንገድ ቁጥጥር ይካሄዳል፡፡ በሰለጠኑና ብቃት ባላቸው የመንገድ ደህንነት ባለሙያዎችና የኦሮሚያ ትራፊክ ፓሊሶች ጋር በቅንጅት በመሆን በ7 ዘመናዊ የፖትሮል ተሽከርካሪዎች ያልተቋረጠ ቁጥጥር ይደረጋል፡፡ በተለያየ ምክንያት በመንገዱ ክልል ውስጥ አደጋዎች ሊከሰቱ ይችላል፡፡ በመሆኑም ለዚህ ተብሎ በተመደቡ የህክምና ባለሙያዎች፣ የአምቡላንስ ተሽከርካሪ ከሙሉ የህክምና መሳሪያዎች ጋር በፍጥነት አደጋ በደረሰበት ቦታ በመድረስ የመጀመሪያ ህክምና እርዳታ ይሰጣል፡፡ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም ለተሻለ ህክምና በአቅራቢያ በሚገኝ የጤና ተቋም በማድረስ ደንበኞች ተጨማሪ ህክምና እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ አገልግሎቱን በስፋትና በጥራት ተደራሸ ለማድረግ የሚተጋው የኢትዮጵያ የክፍያ መንገደች ኢንተርፕራይዝ የደንበኞቹን እርካታ ለመጠበቅ ትልቅ ትኩረት ይሰጣል፡፡ በቀጣይም የተገኙ ተሞክሮዎችን በመቀመር፤ የጥናትና ምርምር ስራዎች በማከናወን፤ የአገልግሎት አሰጣጥ ልዕቀትን በማምጣት በአገልግሎት የረካ ተገልጋይ ለማብዛት ይተጋል፡፡