የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ የ2011 በጀት አመት የ6 ወር አፈፃፀም፡፡

የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ የ2011 በጀት አመት የ6 ወር አፈፃፀም፡፡

የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ በተያዘው የበጀት ዓመት እቅድ አስራ አንድ ስትራቴጂካዊ ግቦች እንዲሁም ስምንት የማስፈጸሚያ ፕሮግራሞችን ነድፎ በመተግበር ላይ ይገኛል፡፡

በስድስት ወራትም 4,234,856 የትራፊክ ፍሰት በማስተናገድ ከክፍያ መንገድ አገልግሎት ብቻ ብር 124,578,594.00 (አንድ መቶ ሃያ አራት ሚሊየን አምስት መቶ ሰባ ስምንት ሺህ አምስት መቶ ዘጠና አራት ብር) ተሰብስቧል፡፡ በተጨማሪም ከልዩ ልዩ ገቢ ብር 6,679,732  በማግኘት በአጠቃላይ 131,258,331 (አንድ መቶ ሰላሳ አንድ ሚሊየን ሁለት መቶ ሃምሳ ስምንት ሺህ ሦስት መቶ ሠላሳ አንድ) ብር መሰብሰብ ተችሏል፡፡

ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመጠቀም አገልግሎት አየሰጠ የሚገኘው የአዲስ አበባ -አዳማ የፍጥነት መንገድ  የላቀ አፈፃፀም ለማስመዝገብ የተፈጠሩ መልካም አጋጣሚዎችን በመጠቀም፤ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በመቋቋም፤ የሚስተዋሉ ድክመቶችን በመቅረፍ፤ ያለውን የሰው ኃይል በዕውቀትና በክህሎት በማሳደግ፤ የአሰራር ስልቶችን በማሻሻል በስፋት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡

ዘመናዊ የክፍያ አሰባሰብ ስርዓት በመጠቀም ለክፍያ መንገድ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ቀልጣፋ አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር የመንገዱን ደህንነት ከማስጠበቅ አኳያ የተለያዩ የግንዛቤ መፍጠሪያ መርሃ ግብሮችን በማዘጋጀት እና በመንገዱ ክልል ውስጥ የሃያ አራት ሰዓት የመንገድ ላይ ቅኝታዊ ቁጥጥር በማድረግ እንዲሁም ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት ላይ ይገኛል፡፡

በተጨማሪም የጥገና አቅምን በማሳደግ ለታሰበለት በአገልግሎት እድሜ ማብቃት እና በአደጋ ምክንያት በንብረቶች ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን በአፋጣኝ በመጠገን የመንገዱ ምቾት እንዳይጓደል እየሰራ ነው በዚህም 191 ቦታዎች ላይ ጥገና በማድረግ በጥቅሉ 4. 04 ኪ.ሜ. የሚሆን የመንገድ አካፋይ እና ዳር የግጭት መከላከያ ብረቶች (Guardrail) ጥገና፤ 460 የመንገድ ዳር አንፀባራቂዎችን የመትከል ሥራ እንዲሁም፤ በ23 ቦታዎች ላይ 175 የብርሃን መከለያ ፓኔሎችን የመትከል ስራ ተሰርቷል፡፡

የአገልግሎት አሰጣጡን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳደገ የሚገኘው ኢንተርፕራይዙ የመንገድ ደህንነትና ዘመናዊ አገልግሎት አሰጣጥን የሚያሳድጉ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ እንቅስቃሴ እያደረገ ሲሆን የመንገድ ላይ መብራት ማስፋፊያ ዝርጋታ፣ የአገልግሎት መስጫ ጣቢያ ግንባታ፣ የከርሰምድር ውሃ ምንጭ ማጎልበቻ፣ የክፍያ አሰባሰብ ስርዓት ማሻሻያ ፤ የፍጥነት ቁጥጥር ስርዓት እንዲሁም የስራ ቦታን ምቹ ከማድረግ አንጻር የማሻሻያ ፕሮጀክቶች የሚጠቀሱ ስራዎች ናቸው፡፡

በፍጥነት መንገድ አስተዳደር የስራ ሂደቱ ከታዩ ችግሮች መካከል የትራፊክ አደጋ ሲሆን ይህም በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለው ችግር አንድ አካል ሆኖ የፍጥነት መንገዱ ላይ የሚስተዋለው ከተፈቀደው ፍጥነት በላይ ማሽከርከር እና አሽከርካሪዎች ቸልተኝነት በዋናነት ይጠቀሳል፡፡

አገልግሎት መስጠት ከጀመረ አራት ዓመት ከሁለት ወር በላይ ያስቆጠረው የአዲስ አበባ -አዳማ      የፍጥነት መንገድ የለተቌረጠ የ24/7 የክፍያ መንገድ አገልግሎት መስጠቱ፤ በኢንተርፕራይዙ የመንገድ አካፋይ ላይ የሚገኙ ንብረቶች በወቅቱ መጠገኑ፤ የድሬዳዋ – ደወሌ የክፍያ መንገድ ስራ ለማስጀመር የዝግጅት ስራዎች ያከናወነ ሲሆን የክፍያ ታሪፍ ዝግጅት፤ የቅርንጫፍ መስሪያ ቤት መዋቅር ፤ የስራ ማስጀመሪያ እቅድ ፤ ባለሙያዎችን በመመደብ የቴክኖሎጂ ዝርጋታ ላይ ሙያዊ ክትትል፣ ድጋፍና ምክረ-ሃሳብ የመስጠት ስራ እየተሰራ ይገኛል፤

የድሬደዋ ደወሌ የክፍያ መንገድ ባለድርሻ አካላት ከሆኑት ፣ ከሱማሌ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ፣ ከሽንሌ ዞን አስተዳደር እና የክፍያ መንገዱን ከሚያዋስኑ ሁሉም ወረዳ አመራሮች፣ መንገዱን ከሚያዋስኑ ኡጋዞች እና የሀገር ሽማግሌዎች፣ ከድሬዳዋ ከተማ የመንግስት ሃላፊዎች እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር ስለ ክፍያ መንገዱ አሰራርእና የሚጠበቁ የትብብር ሁኔታዎች ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡

በቀጣይም የድሬደዋ ደወሌን የክፍያ መንገድ ስራ ለማስጀመርና በስድስት ወራት የታዩ ደካማ ጎኖችን በማየትና ማስተካከያ በማድረግ የነበሩ ጠንካራ ጎኖችን ከዚህ በተሻለ በማጎልበት የኢንተፕራይዙን ራዕይ ከግብ ማድረስ እንደሚገባ አቅጣጫ  ተቀምጧል፡፡