ድሬዳዋ- ደወሌ የክፍያ መንገድ

ድሬዳዋ- ደወሌ የክፍያ መንገድ

ድሬዳዋ- ደወሌ የክፍያ መንገድ

በሀገራችን በክፍያ መንገዶች ታሪክ የመጀመሪያ የሆነው እና የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ የሚያስተዳድረው የአዲስ አበባ- አዳማ የክፍያ መንገድ አገልግሎት በመስጠት ረገድ ቀዳሚው ነው፡፡ መስከረም 2007 ዓ.ም አገልግሎት መስጠት የጀመረው የክፍያ መንገድ በአሁኑ ወቅት በቀን በአማካይ ከ23 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎችን የማስተናገድ አቅም ላይ ደርሷል፡፡ የፍጥነት መንገድ ለሀገራችን አዲስ ተሞክሮ ቢሆንም ፈጣን መንገዱ ከአስገኘው ጠቀሜታ አንጻር ተመራጭ እንዲሆን አድርጐታል፡፡

በመሆኑም መንግስት የክፍያ መንገዶችን ማስፋፋት የሚኖረውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ በመረዳት በሀገራችን ሁለተኛ የሆነውን የድሬደዋ- ደወሌ የክፍያ መንገድ ግንባታ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ክፍት ማድረግ ችሏል፡፡

ከአዲስ አበባ- አዳማ ቀጥሎ አገልግሎት የሚሰጠው የድሬደዋ- ደወሌ የክፍያ መንገድ በምስራቅ የኢትዮጵያ ክፍል የሚገኝ ሲሆን ለጅቡቲ የባህር ወደብ የመንገድ ትራፊክ እንቅስቃሴ ማሳለጫነት ጉልህ ሚና ያለው ነው፡፡ ከአዋሽ- ሚሌ- ጅቡቲ ወጪ ገቢ መንገድ አንፃር 50 ኪ.ሜ ቅርበት ያለው መሆኑ፤ ከድሬደዋ- ደወሌ ለጉዞ ይፈጅ የነበረውን ጊዜ መቀነሱ፤ ለአካባቢው ህብረተሰብም ከ200 በላይ የስራ ዕድል መፍጠሩ፤ ከመንገዱ የሚገኙ ጥቅሞች ናቸው፡፡

መንገዱ በከተሞች መካከል ምቹ የትራንስፖርት ስርዓት በመፍጠር የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ያጠናክራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በዚህም በዋናነት ድሬደዋ፣ ለገሙዲ፣ ሃርሙካሌ፣ አይሻና የድንበር ከተማ የሆነችውን ደወሌን በማስተሳሰር ረገድ ትልቅ አስተዋፅኦ ያደርጋል፡፡

ሀገራችን ከፍተኛ የውጪ ንግድ ከምታካሂድባቸው የባህር በሮች የጅቡቲ ወደብ ዋነኛ ነው፡፡ በዚህም በየዕለቱ በርካታ ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች ጉዟቸውን በዚህ መንገድ ያደርጋሉ፡፡ ስለሆነም በርካታ ከባድ ተሽከርካሪዎች የክፍያ መንገዱን ስለሚጠቀሙ በየዕለቱ በአማካይ 860 ተሽከርካሪዎች ይስተናገዳሉ፡፡ እስካሁን ባለው አገልግሎት በቀን በአማካይ 160 ሺህ ብር ይሰበሰባል፡፡ ይህንንም የትራፊክ ፍሰት በተቀላጠፈ መልኩ ለማስኬድ ያስችል ዘንድ በሶስቱም የክፍያ ጣቢያዎች 12 የመግቢያ እና 12 የመውጫ በሮች በአጠቃላይ 24 የክፍያ በሮች አሉት፡፡

ሰኔ 9/2011 ዓ.ም አገልግሎት መስጠት የጀመረው የድሬደዋ- ደወሌ የክፍያ መንገድ 5.2 ቢሊየን ብር በሆነ ወጪ የተገነባ ነው፡፡ የፈጣን መንገዱ ግንባታ 85% ከቻይናው ኢምፖርት ኤክስፖርት ባንክ በተገኘ ብድር እንዲሁም ቀሪው 15% ደግሞ በኢትዮጵያ መንግስት የተሸፈነ ሲሆን፤ ግንባታው ሲ ጂ ሲ/CGC/ በተባለ የቻይና ተቋራጭ የተከናወነ ነው፡፡

የድሬደዋ ደወሌ የክፍያ መንገድ 223 ኪ.ሜ ርዝመት እንዲሁም በዲዛይን ደረጃ 3 (DS3) የተገነባ ሲሆን 7ሜ ስፋት አለው፡፡ እያንዳንዱ የመጓጓዣ መስመር 3.5 ሜ ሲሆን በመንገዱ ግራና ቀኝ የሚገኘው የአስፋልት ትከሻ (Asphalt shoulder) 45 ሳ.ሜ ስፋት አለው፡፡

በሀገራችን በአንድ ተቋራጭ የተገነባ በርዝመቱ የመጀመሪያ የሆነው የድሬደዋ- ደወሌ የክፍያ መንገድ በአመዛኙ ከባድ የተሽከርካሪዎችን የሚያስተናግድ እንደመሆኑ ክብደት ቁጥጥር ስርዓት መኖሩ፤ በሶስቱም ጣቢያዎች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ የክፍያ አሰባሰብ ስርዓት መዘርጋቱ እንዲሁም የተደራጀ የክፍያና ትራፊክ የቁጥጥር ስርዓት (monitoring system) መኖሩ መንገዱን ዘመናዊ ያደርጉታል፡፡

መንገዱ ለ17 ዓመታት እንዲያገለግል ታስቦ የተገነባ ስለሆነ ከልክ በላይ ጭነት በያዙ ተሽከርካሪዎች ጉዳት እንዳይደርስበት እና ከታሰበለት የአገልግሎት ዘመን ቀድሞ ግልጋሎት መስጠት እንዳያቆም በሶስቱም የክፍያ ጣቢያዎች ዘመናዊ የክብደት መቆጣጠሪያ ሚዛኖች ለአገልግሎት ዝግጁ ተደርጓል፡፡

ኢንተርፕራይዙ ከሚያስተዳድራቸው የክፍያ መንገዶች ሁለተኛው የሆነው የድሬደዋ- ደወሌ መንገድ የተገልጋይን ፍላጐት በጠበቀ መልኩ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅቱን አጠናቆ ስራ ጀምሯል፡፡ የአገልጋይነት መንፈስ በተላበሱ ሰራተኞች አማካኝነት ቀልጣፋ አገልግሎት የሚሰጠው ይህ የክፍያ መንገድ በድሬደዋ- ደወሌ የክፍያ መንገድ ክፍት ሞዴል (open model) የክፍያ ስርዓት አይነት በመጠቀም ክፍያ እንዲፈፀም ይደረጋል፡፡

የክፍያ መንገዱ ለቀላል ተሽከርካሪ 100፣ ለመካከለኛ 150፣  ለከባድ ተሽከርካሪ 200፤ ለተሳቢ ተሸከርካሪዎች 250 ብር ታሪፍ እንዲከፍሉ ተወስኗል፡፡

የክፍያ መንገዱም በ2012 በጀት ዓመት 438 ሺህ ተሽከርካሪዎች በማስተናገድ ብር 80,832,411 (ሰማኒያ ሚሊየን ስምንት መቶ ሰላሳ ሁለት ሺህ አራት መቶ አስራ አንድ) ገቢ ያስገኛል ተብሎ ዕቅድ ተይዟል፡፡

የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝም ለ5 ዓመታት ሲያስተዳድረው ከቆየው የአዲስ አበባ- አዳማ የክፍያ መንገድ ተሞክሮዎችን በመውሰድ የድሬደዋ-ደወሌ የክፍያ መንገድን በተቀላጠፈ መልኩ አገልግሎት እንዲሰጥ ያደርጋል፡፡

 ደህንነትዎ የክብር ስማችን ነው!