የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ የ2011 በጀት አመት ዕቅድ አፈፃፀም

የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ የ2011 በጀት አመት ዕቅድ አፈፃፀም

የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ የ2011 በጀት አመት ዕቅድ አፈፃፀም

የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ 2011 የበጀት ዓመት እቅድ 11 ስትራቴጂካዊ ግቦች ነድፎ ሲተገብር ቆይቷል፡፡

በበጀት ዓመቱም 8,487,743 የትራፊክ ፍሰት በማስተናገድ ከክፍያ መንገድ አገልግሎት ብር 264,307,134 (ሁለት መቶ ስልሳ አራት ሚሊየን ሶስት መቶ ሰባት ሺ አንድ መቶ ሰላሳ አራት) ተሰብስቧል፡፡ በተጨማሪም ከልዩ ልዩ ገቢዎች (ከማስታወቂያ ቦታዎች ኪራይ፣ ከተሽከርካሪ ማንሻና መጎተቻ…) ብር 11,276,468 (አስራ አንድ ሚሊየን ሁለት መቶ ሰባ ስድስት ሺህ አራት መቶ ስልሳ ስምንት) በመሰብሰብ በ2011 በጀት ዓመት በአጠቃላይ ብር 275,583,602 (ሁለት መቶ ሰባ አምስት ሚሊየን አምስት መቶ ሰማንያ ሶስት ሺህ ስድስት መቶ ሁለት) መሰብሰብ ተችሏል፡፡

የመንገዱን ደህንነት ከማስጠበቅ አኳያ የተለያዩ የግንዛቤ መፍጠሪያ መርሃ ግብሮችን በማዘጋጀት እና በመንገዱ ክልል ውስጥ የ24 ሰዓት የመንገድ ላይ ቅኝታዊ የትራፊክ ቁጥጥር በማድረግ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ተሰርቷል፡፡ በተጨማሪም የጥገና አቅምን በማሳደግ በአገልግሎት እድሜ ማብቃት እና በአደጋ ምክንያት በንብረቶች ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን  በመጠገን የመንገዱ ምቾት እንዳይጓደል እየሰራ ነው፡፡

የአገልግሎት አሰጣጡን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳደገ የሚገኘው የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ በቀጣይ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እያደረገ ሲሆን የመንገድ ላይ መብራት ማስፋፊያ ዝርጋታ፣ የአገልግሎት መስጫ ጣቢያና የደንበኞች የጥሪ ማዕከል ግንባታ፣ እንዲሁም የስራ ቦታን ምቹ (Ergonomic) ከማድረግ አንጻር የማሻሻያ ፕሮጀክቶች ታቅደው በመከናወን ላይ ናቸው፡፡

አገልግሎት መስጠት ከጀመረ አምስት አመት ያስቆጠረው የአዲስ አበባ- አዳማ የፍጥነት መንገድ ያልተቌረጠ የ24 ሰዓት የክፍያ መንገድ አገልግሎት መስጠቱ፤ የድሬዳዋ- ደወሌ የክፍያ መንገድን ስራ ማስጀመሩ፤ በመንገዱ አካፋይ ላይ የሚገኙ የመንገድ ሀብቶች በወቅቱ መጠገኑ፤ ውጤታማና ዘመናዊ የሆነ የአረንጓዴ ልማት ፕሮግራም መተግበሩ ጠንካራ ጎኖች ሆነው ተነስተዋል፡፡ በበጀት አመቱ የውጤት ተኮር ስርዓት ዕቅድ አፈፃፀም ምዘና አጠቃላይ ውጤት 88.16 ሲሆን የአፈፃፀም ደረጃውም ከፍተኛ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

በቀጣይም በበጀት ዓመቱ የታዩ ደካማ ጎኖችን በጥልቀት በመመርመርና ማስተካከያ በማድረግ፤ የነበሩ ጠንካራ ጎኖችን በማዳበር እንዲሁም ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀስ የኢንተፕራይዙን ራዕይ ከግብ ማድረስ እንደሚገባ አቅጣጫ  ተቀምጧል፡፡