በአዲስ አዳማ የፍጥነት መንገድ ላይ የፍጥነት መቆጣጠሪያ የራዳር ቴክኖሎጂ ሊተገበር ነው

በአዲስ አዳማ የፍጥነት መንገድ ላይ የፍጥነት መቆጣጠሪያ የራዳር ቴክኖሎጂ ሊተገበር ነው

አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 21 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አዳማ የፍጥነት መንገድ ላይ የፍጥነት ገደብን የተመለከቱ የትራፊክ ህጎችን ለማስተግበር የሚያስችል አዲስ የራዳር ቴክኖሎጂ ከቀጣዩ አመት ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል ተባለ።

78 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የአዲስ አዳማ የፍጥነት መንገድ፥ ለከባድ ተሽከርካሪዎች በሰዓት 80፣ መካከለኛ መንገዱን ለሚጠቀሙ በሰዓት 100 ኪሎ ሜትር እንዲሁም ደርቦ ማለፊያ መንገዱን ለሚጠቀሙት ደግሞ 120 ኪሎ ሜትር በሰዓት የፍጥነት ገደብ ተቀምጦለታል።

ከኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ እና ከኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው በርካታ አሽከርካሪዎች ህጉን በአግባቡ ተግባራዊ አያደርጉም።

በዚህም በ2007 አመተ ምህረት 21፣ በ2008 ዓ.ም 28 እንዲሁም በተጠናቀቀው በጀት አመት ደግሞ 20 ሰዎች ለሞት ተዳርገዋል።

የተቀመጠውን የፍጥነት ወሰን አክብሮ አለማሽከርከርና የተሽከርካሪ የቴክኒክ ብቃትን ያላገናዘበ ፍጥነት መጠቀም ለአደጋዎቹ በምክንያትነት ይነሳሉ።

በሶስት አመታት ውስጥ ብቻ ለ69 ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነውን ይህን ችግር ለመቅረፍም፥ ኢንተርፕራይዙ ከኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመሆን በ2010 የቁጥጥር ስራውን እንደሚያጠናክር ገልጿል።

ለዚህም ኢንተርፕራይዙ በተመረጡ ቦታዎች ላይ ዘመናዊ የፍጥነት መቆጣጠሪያ ራዳሮችን እንደሚተክል አስታውቋል።

በኢንተርፕራይዙ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና መረጃ ቁጥጥር ቡድን ሃላፊ አቶ ታገል አያሌው እንደሚሉት፥ የራዳር ቴክኖሎጂው በተመረጡ አካባቢዎች በመንገዱ ግራና ቀኝ መተላለፊያዎች ላይ በእያንዳንዱ መስመር ላይ የሚተከል ነው።

ይህም የመንገዱን ደህንነት ለማስጠበቅ እንደሚያስችል ጠቅሰው፥ የቁጥጥር ስራውን ለማገዝ የመንገድ ላይ ካሜራዎች በተጨማሪነት እንደሚተከሉም ገልጸዋል።

በኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የትራፊክ ደህንነት ቁጥጥር ባለሙያ ምክትል ኮማንደር ንጉሴ ግርማ በበኩላቸው፥ ራዳሩ በትራፊክ ፖሊስ እጅ ከሚያዘው አንጻር የእይታ ግርዶሽን ስለሚከላከል የመንገድ ደህንነት ህጎችን በቀላሉ ለማስተግበር ያስችላል ብለዋል።

በመንገዱ ላይ የራዳር ቴክኖሎጂዎችን ከመተግበር ባለፈም በደም ውስጥ የሚገኝ የአልኮል መጠን ፍተሻ እንደሚጀመርም ምክትል ኮማንደር ንጉሴ ተናግረዋል።

ይህም ጠጥተው የሚያሽከረክሩ ሰዎችን በመቆጣጠር አደጋን መቀነስ ያስችላል ነው ያሉት።

 

 

 

 

 

በዓላዛር ታደለ