ችግኞችን ከመትከል ባሻገር በዘላቂነት መንከባከብ ይገባል-ፕሬዝዳንት ሙላቱ

ችግኞችን ከመትከል ባሻገር በዘላቂነት መንከባከብ ይገባል-ፕሬዝዳንት ሙላቱ

አዲስ አበባ ሃምሌ 15/2009  የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂው ግቡን እንዲመታ ችግኞችን ከመትከል ባሻገር መንከባከብ እንደሚገባ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ አሳሰቡ።

የኢትዮጵያ ክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ የ2009 ዓ.ም ዓመታዊ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ፕሬዝዳንቱ በተገኙበት በአዲስ -አዳማ የፍጥነት መንገድ ዳርቻ ተካሂዷል።

ፕሬዝዳንቱ በዚሁ ወቅት እንዳሉት በአገሪቱ ሲካሄድ የቆየው የደን ጭፍጨፋ 40 በመቶ የነበረውን የድን ሽፋን ወደ 3 በመቶ ዝቅ እንዲል አድርጓል።

”ይህም ለድርቅና ተያያዥ የድህነት ገጽታዎች ታጋላጭ እንድንሆን አድርጓል” ያሉት ፕሬዝዳንቱ ችግኞችን ከመትከል ባለፈ በዘላቂነት መንከባከብ የሁሉም የቤት ሥራ ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

መንግሥት በአረንጓዴ ልማቱ ስትራቴጂዎችን ቀይሶ ህዝቡን በማሳተፍ እያደረገ ያለው ርብርብ ውጤት በማምጣት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

በአንድ ዓመት ብቻ ከአስምት ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል ስኬታማ ስራ መከናወኑን የገለጹት ፕሬዘዳንቱ  በየዓመቱ  በተከናወኑ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች የደን ሽፋኑን ወደ 15 በመቶ ከፍ እንዲል አድርጎታል ብለዋል።

የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝም በአዲስ አዳማ ፍጥነት ግራና ቀኝ ዳርቻዎች የሚተክላቸው ችግኞች ከተሽከርካሪዎች የሚለቀቀውን የካርቦን ጋዝ የሚቆጣጠር በመሆኑ ለተስማሚና  ንጹህ አየር መር ትልቅ ዋጋ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

መሰል የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሮች ላይ የአካባቢውን ህዝብ በስፋት በማሳተፍ የአረንጓዴ ልማት ስራውን ማፋጠን  እንደሚገባም አሳስበዋል።

የኢንተርፕራይዙ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙስጠፋ ከድር በበኩላቸው ኢተርፕራይዙ ባለፉት ሁለት ዓመታት በፍጥነት መንገዱ ግራና ቀኝ 35 ሺህ ችግኞችን በመትከልና በመንከባከብ አገራዊ ኃላፊነቱን ሲወጣ ቆይቷል።

በቀጣይም የተተከሉና የሚተከሉ ችግኞችን ከፍጥነት መንገዱ አዋሳኝ ነዋሪዎች ጋር በመተባበር የመንከባከቡ ሥራ ተጣንክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትር ደኤታ አቶ ከበደ ይማም እንደገለጹት በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች በሚከናወኑ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ስራዎች የአገሪቱን የደን ሽፋን በ2022 ዓ.ም ወደ 30 በመቶ ከፍ ለማድረግ እቅድ ተይዟል።

በተያዘው ዓመት በአገር አቀፍ ደረጃ 1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በደን ለመሸፈን እቅድ መያዙን ገልጸው 3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ችግኝ ለዚሁ ተግባር ዝግጁ መደረጉን አብራርተዋል።