የሞጆ – ባቱ የክፍያ መንገድን ስራ ለማስጀመር የቅድመ ዝግጅት ስራ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ አስታወቀ ፡፡ 

የሞጆ – ባቱን 92 ኪ.ሜ የክፍያ መንገድ ስራ ለማስጀመር ከአስተዳደራዊ ስራዎች ባሻገር የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደቱን ቀልጣፋና ደህንነቱ የተጠበቀ ለማድረግ ከህብረተሰቡ ጋር እንዲሁም ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር ውይይት ተካሄደ፡፡

ኢንተርፕራይዙ ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ጋር በቅንጅት ባዘጋጀው በዚህ የውይይት መድረክ የተቋማቱ ሃላፊዎች እና በመንገዱ አዋሳኝ ያሉ የከተሞች አስተዳደሪዎች የፀጥታ መዋቅር ሃላፊዎች፣ የሞጆ-ባቱ የፍጥነት መንገድ አቅራቢያ የሚገኙ ነዋሪዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል ፡፡

የኢንተርፕራይዙ ስራ አስኪያጅ፤የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ተወካዮች የኦሮሚያ ፖሊስ ም/ኮሚሽነር፣ ሌሎች የስራ ሃላፊዎች ከተሰብሳቢው ጋር ውይይት ያደረጉ ሲሆን የሞጆ-ባቱ የፍጥነት መንገድ የሚያስገኛቸው ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጠቀሜታዎች በማንሳት የአካባቢው ህብረተሰብ የመንገዱን ሃብት እንደራሱ በመጠበቅ መንገዱ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጥ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ እና ከሚመለከተው አካላት ጋር በቅንጅት እንዲሰሩ ጠይቀዋል ፡፡

ተሳታፊዎችም የመንገዱ ግንባታ ለአካባቢው ሁለንተናዊ እድገት ያለውን አስተዋፅኦ ተረድተው የበኩላቸውን እንደሚወጡ የገለፁ ሲሆን ከግንባታው ጋር ተያይዘው መስተካከል ያለባቸውን አንዳንድ ስራዎች እንዲሁም የአካባቢውን ነዋሪዎችን በዘላቂነት ተጠቃሚ የሚያደርጉ ጉዳዮች ታሳቢ እንዲደረጉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በመጨረሻም የኢንተርፕራይዙ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሙስጠፋ አባሲመል የሞጆ-ባቱ የፍጥነት መንገድ በከፍተኛ ወጪ የተገነባ እንደመሆኑ ሁሉም በባለቤትነት ሊጠብቀው እንደሚገባ ገልፀው ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣንም ሆነ ከኦሮሚያ ፖሊስ ኮምሽን ጋር ለስራው ስኬታማነት በጋራ እንደሚሰሩ ገልፀዋል፡፡