የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ለሃገር መከላከያ ሰራዊት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠሉን ገለፀ፡፡

የኢትዮጵያን ሰላም ለማረጋገጥ እና የሃገርን ድንበር ለማስከበር ለሚዋደቁት ጀግና የሃገር መከላከያ ሰራዊት የሚደረገው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የኢትዮጵያ የክፍያ መንገደች ኢንተርፕራይዝ ገለፀ፡፡
ኢንተርፕራይዙ በሶስቱም የክፍያ መንገድ ቅርንጫፎች የሚገኙ ሰራተኞችን በማወያየትና በማስተባበር እያንዳንዳቸው የ1 ወር ደመወዛቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ በማወያየት ተፈፃሚ ማድረጉ የሚታወስ ነው፡፡
ከዚህም ባሻገር ሃገርን ለማዳን ግዳጅ ላይ የነበሩና ጉዳት ለደረሰባቸው የሃገር መከላከያ ሰራዊት አባላት የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ በማገገሚያ ጣቢያ በመገኘት ከ750 ሺህ ብር በላይ የሚያወጣና ለ600 የሰራዊቱ አባላት የሚሆን የአልባሳት ስጦታን በማበርከት ማህበራዊ ሃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ እንደሚገኝም አስታውቋል፡፡
ድጋፉን ለማበርከት በዕለቱ የተገኙት የክፍያ መንገዱ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሙስጠፋ አባሲመል እንደገለፁት በሃገር ላይ ለተጋረጠው የህልውና አደጋ ውድ ሕይወታቸውን ለሰዉልንም ሆነ ጉዳት ደርሶባቸው በማገገም ላይ ላሉት የመከላከያ አባላት የሚደረገው ድጋፍ ለከፈሉት መስዋትነት የሚመጥን ባይሆንም ተቋሙ የድርሻውን ለመወጣት ያደረገው መሆኑን ገልጸው፡፡ በቀጣይም ለመከላከያ ሰራዊቱ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡