የአረንጓዴ ልማት

የአረንጓዴ ልማት

አረንጓዴ ልማት የአንድ ሀገር እድገት መገለጫ ነው፡፡  የአረንጓዴ  ልማት  የከተማ  የአየር  ለውጥ አይበገሬ  ኢኮኖሚ ለመገንባት  ያስችላል፡፡  ልማቱ በተገቢው ሁኔታ  ከለማ  ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ የአረንጓዴ  ልማት  አካባቢን  ውብና ምቹ  እንዲሁም  ለሰው ልጆች ተስማሚ  አየርን  በመስጠት  የተረጋጋ  ኑሮን ለመኖር ያስችላል፡፡

የአረንጓዴ  ልማት  ጉዳይ  የ21ኛው ክፍለ ዘመን  አጀንዳ እየሆነ መጥቷል፡፡ የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ አሁን አሁን  የሰው ልጆች ከሚፈልጉት  ውጭ  በመሆን  መስመሩን  ቀይሯል፡፡ የዓለም የደን ሽፋን  ከባለፉት  ሁለት አስርት ዓመታት  ወዲህ  እየሳሳ መምጣቱ  ለሙቀት መጨመር  ከፍተኛ  አስተዋፅኦ  እያደረግ ነው፡፡ ለዚህ ሁሉ ለውጥ  በምክንያትና  በዋነኛነት  የሚጠቀሱት  ሰው ሰራሽና  ተፈጥሯዊ ጉዳዮች  ናቸው፡፡

የአረንጓዴ ልማት ፖሊሲ  የተለያ ሃገራት  ቀርፀው  የአካባቢያቸውን  ስነ-ምህዳር፣ ብዛ ህይወትና የአየር ንብረትን  ለሰውና ለእንስሳት  ምቹ ለማድረግ  እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ ያደጉት ሃገራት ለደረሱበት ኢኮኖሚያዊ ለውጥ እና እድገት እንደአንድ ምክንያት የሚጠቀሰው   አካባቢ ላይ ትልቅ ትኩረት  ሰጥተው  በመስራታቸው ነው፡፡ የአረንጓዴ ልማትን ማስፋፋት  ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዳለ ሆኖ  የአየር ንብረትን  ሚዛናዊ  በማድረግ ረገድ  የጎላ  ድርሻ  ይኖረዋል፡፡ ከዚህም ከፍ ሲል  ጤናማ ማህበረሰብን  ለመገንባት  ወሻኝ  ድርሻ አለው፡፡

 

ከዛሬ ሁለት አስርት ዓመታት  በፊት  የሃገራችን  የደን ሽፋን  40 ከመቶ ያህሉ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ እንደሌሎች  አገራት  የደን መሳሳትና  የአየር ንብረት ለውጥ  ተጋላጭ ሆናለች፡፡ ሀገሪቱን የገጠማትን  የደን  መሳሳት ችግር ወደ ነበረበት  ለመመለስና እንዲያገግም ለማድረግ  መጠነ ሰፊ ስራዎች  በመንግስትና  በህዝብ ተሳትፎ  እየተሰራ ይገኛል፡፡ ሀገሪቱ ለአየር ንብረት ለውጥ  የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ   በላቀ ደረጃ   ለመፈፀም  የሚያስችሉ  ዘርፍ አቀፍ ስልት  ዝግጅት እያደረገች ነው፡፡ በዚህም እያሳሳ የመጣውን  የደን ሽፋን ለመመለስ  በተደረገው ጥረት  በመጀመሪው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን  እቅድ  በቢሊየን የሚቆጠሩ ችግኞችን በተለያ የሀገሪቱ  ከተሞችና መንደሮች  ተተክለዋል፡፡ ከተተከሉት  በቢሊየን   የሚቆጠሩ  ችግኞች  መካከል 40 ከመቶ  ያህሉን በማፅደቅ  አሁን ያለውን  የሀገሪቱ  የደን ሽፋን 15.5 ከመቶ ለማድረስ ተችሏል፡፡ ይህንን ሂደት ለማስቀጠልም  በሁለተኛው የእድገትና ትራንሰፎርሜሽን  እቅድ  4 ቢሊየን  ችግኞችን በመላው ሀገሪቱ  የመትከልና የማጽደቅ እቅድ  ታቅዷል፡፡

 

የመጀመሪያ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ትሩፋት የሆነው የአዲስ አበባ አዳማ  የፍጥነት መንገድ አገራዊ እቅዱን መሰረት በማድረግ  ከመንገዱ ግንባታ  ጀምሮ  የተለያዩ የአካባቢ ጥበቃና  የአረንጓዴ ልማት ስራዎችን  በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ ኢንተርፕራይዙ ወደ ዛፍ  የሚቀየሩ ችግኞችን  በመትከል  ወደ ደንነት የመቀየር  አላማን አንግቧል፡፡ ኢንተርፕራይዙ በተፈጥሮ ህብረቀለማት ባሸበረቁ ችግኞች  የፍጥነት መንገዱንና ስድስቱንም  የክፍያ ጣቢያዎች  ለማስዋብ  ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡

 

78ኪ.ሜ በሚሸፍነውየአዲስ አበባ- አዳማ የፍጥነት መንገድ ውስጥ  በመንገዱ አካፋይ/ Median/  እና በመንገዱ ግራና ቀኝ  ዳር ላይ  እንዲሁም በስድስቱም  የክፍያ ጣቢያዎች  የተለያዩ  ዓይነት  ችግኞችን  የመትከል፣ የመንከባከብና  የማፅደቅ  ስራ በማከናወን ላይ ነው፡፡ በፍጥነት መንገዱ የሚካሄደው  የአካባቢና የአረነጓዴ ልማት  ዋነኛው  ዓላማ  ለመንገዱ ተጠቃሚዎች  መንገዱን ምቹና ውብ  ከማድረግ ባሻገር  የአካባቢውን የአየር ንብረት  ለአካባቢው ነዋሪዎችና  ለመንገዱ ተጠቃሚዎች ተስማሚ ለማድረግ  እንዲሁም የካርበን ልቀትን ( የአካባቢ ብክለትን) ለመቀነስ  ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ከዚህም ሌላ ችግኞችን የመትከልና የማፅደቅ ስራው የመንገዱ ተጠቃሚዎች  በምሽት  ሲያሽከረክሩ ከተቃራኒ አቅጣጫ የሚመጣውን  መብራት በመከላከል የትራፊክ   አደጋን ለመቀነስ  እንዲችሉ  ለማድረግ ነው፡፡ ለአይንም ደስ የሚል እይታን ለመፍጠርና  መንፈስን ለማደስ  ብሎም አሽከርካሪዎች  የእንቅልፍና  የድካም ስሜት ሲሰማቸው ንፁህ አየር እንዲያገኙና ተነቃቅተው  እንዲያሽከረክሩ በማድረግ  ብርቱ ጥረት  እየተደረገ ነው፡፡

 

ኢንተርፕራይዙ ስራ ከጀመረበት  ጊዜ ጀምሮ    በአረንጓዴ ልማት  ብዙ ርቀትን  ተጉዟል፡፡ ለአረንጓዴ ልማቱ የሚጠቅሙ ግብዓቶችን  በሟሟላት  ችግኞችን  ለማፅደቅ  ከፍተኛ ጥረት  እያደረገ ነው፡፡ ችግኞችን ለማልማት  ከአካባቢው የሚገኘውን  ውሃ የሚጠቀም ሲሆን  በቀጣይም  አየር ንብረቱን ታሳቢ ያደረጉ  የውሃ  እጥረቶች ሊያጋጥሙ  ስለሚችሉ   በመመንገዱ ክልል  ውስጥ የውሃ ማበልፀግ  ስራ ተከናውኗል፡፡

ኢንተርፕራይዙ  በተጠናቀቀው  በ2008 በጀት ዓመት  በአረንጓዴ ልማት ስራ  በመንገዱ ግራና ቀኝ  በሁለቱም አቅጣጫ ማለትም  ከአዲስ አበባ- አዳማ  እስከ 38 ኪ.ሜ  እንዲሁም  ከአዳማ አዲስ አበባ  27 ኪ.ሜ  ላይ   25 ሺህ ችግኞችን  የማፅደቅና  የእንክብካቤውን   ስራ እየሰራ ነው፡፡ ችግኞችን የማፅደቅና  የእንክብካቤውን ስራ  በይበልጥ   ውጤታማ  ለማድረግ  23000 ጉድጓዶችን  በማዘጋጀት  በአረንጋዴ ልማት  እንደሃገርና  እንደተቋም  ለውጥ ለማምጣት   በጥሩ  ግስጋሴ  ላይ  ይገኛል፡፡

ችግኞችን   በመንከባከብ  ዘርፍም  ችግኞች  በተለያየ ምክንያት  ሲጎዱ  ሌላ በምትኩ  የሚተካ ሲሆን  ዘንድሮም  በመንገዱ አካፋይ / Median/ ላይ  የሚገኙ ችግኞች በመጎዳታቸው ምክንያት  13 ሺህ   ችግኞችን  የመተካት ስራ  ተሰርቷል፡፡ ኢንተርፕራይዙ  የአረንጓዴ ልማት ላይ  ልዩ ትኩረት አድርጎ ስለሚሰራ   ከባለፈው በጀት ዓመት  በንፅፅር ሲታይ  የዘንደሮ ስራ  የተሳካ ነበር ለማለት ይቻላል፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆነው  በመንገዱ  አካፋይ  ላይ የሚገኙት  ችግኞች  ፀድቀው የአካባቢውን አየር  ነፋሻማ በማድረግ  ውብና ማራኪ እይታን ለአሽከርካሪዎች ፈጥረዋል፡፡   ኢንተርፕራይዙ  የአረንጓዴ ልማት  ላይ  ልዩ ትኩረት  ሰጥቶ የሚሰራው ይህ የፍጥነት  መንገድ  በአገሪቱ ለሚስፋፉት የፍጥነት መንገዶች  ሞዴል  እንዲሆን  ለማድረግ በማለም  ነው፡፡

 

ከዚህ በተጓዳኝም ሌሎች  ያደጉት  ሃገራት  እንደሚያደርጉት  ኢንተርፕራይዙ የመንገዱን ውበት ለመጠበቅ  ዘርፈ ብዙ  ስራዎችን  እያከናወነ ነው፡፡ የፍጥነት  መንገዱን ውብና  ንፁህ ለማድረግ  የተለያዩ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች  ይሰራል፡፡ እነዚህም ፅዳትን በተመለከተ  የአስፓልት እና   በመንገዱ ግራና ቀኝ  ቦታዎች  ላይ የፅዳት  ስራ ሁልጊዜም   የሚከናወን  ተግባር ሲሆን  አረም የማንሳት  በሁለቱም አቅጣጫዎች  “በየሌባዩ ” ተመሳሳይ  ተግባር  ይሰራል፡፡ ከዚህም ሌላ  መንገዱን ተከትሎ ያሉት የውሃ መውረጃዎች ( ቦዮች) ለአፍታ እንኳን ሳይቋረጡ  ይፀዳሉ፡፡ የቢሮና የግቢ ማስዋብ ስራም  በስድሰቱም የክፍያ ጣቢያዎች  እየተሰሩ ሲሆን  በቱሉዲምቱ ዋና  የክፍያ ጣቢያ  ከ100 በላይ  የቢሮ አበባ  በተጠናቀቀው በጀት ዓመት  በማስገባት  የማስዋብ  ስራ ተከናውኗል፡፡

 

ኢንተርፕራይዙ  በቀጣይ 2009  በጀት ዓመት  ከአዲስ አበባ  ፅዳትና ውበት መናፈሻ ጋር  በመተባበር  የደረቅና  የፈሳሽ  ቆሻሻ  ማስወገጃ  በዘላቂነት   ውጤታማ  ስራ  ለመስራት ታቅዷል፡፡ በአረንጓዴ ልማትና እንክብካቤ ዘርፍም  ከግብርና ሚኒስቴር ጋር  በመቀናጀት  ችግኝና ሌሎች ግብርና ነክ  የሆኑ ስራዎችን  ለመስራት በሂደት ላይ ነው፡፡

የአረንጓዴ ልማትን ለማስቀጠልና ተጨባጭ  የሆነ  ለውጥ በዘርፉ ለማምጣት   እንዲሁም  በአገር አቀፍና  በተቋም ደረጃ  የታሰበውን  የአረንጓዴ ልማት  ከግብ ለማድረስ  የሁሉም ዜጋ ርብርብን ይጠይቃል፡፡