የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ በ2014 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ከስድስት መቶ ሃያ ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ሰበሰበ፡፡

የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ስራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ያልተቋረጠ የ24/7 አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ አገልግሎቱን ያለማቋረጥ የሚሰጠው ይህ ተቋም ቀልጣፋና ዘመናዊ በሆነ መልኩ የተጠቃሚዎቹን ፍላጎት ለማሟላት የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ በበጀት ዓመቱ በአዲስ- አዳማ ፤ በሞጆ ባቱ እና በድሬዳዋ- ደወሌ የክፍያ መንገዶች 11,291,490 የትራፊክ ፍሰት ለማስተናገድ አቅዶ 11,337,483 ማከናወን ችሏል፡፡ ክንውኑም 100.4 % ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

ኢንተርፕራይዙ ከመንገዱ ተጠቃሚዎች አገልግሎት ብር 493,722,625 (አራት መቶ ዘጠና ሶስት ሚሊየን ሰባት መቶ ሃያ ሁለት ሺህ ስድስት መቶ ሃያ አምስት)ለመሰብሰብ አቅዶ 553,322,756 (አምስት መቶ ሃምሳ ሶስት ሚሊየን ሶስት መቶ ሃያ ሁለት ሺህ ሰባት መቶ ሃምሳ ስድስት) ተሰብስቧል፡፡ በዚህም ክንውኑ 111.5 % ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ እንዲሁም ከልዩ ልዩ ገቢዎች (ከማስታወቂያ ቦታዎች ኪራይ፣ ከተሽከርካሪ ማንሻና መጎተቻ…) ብር 66,864,801 (ስድሳ ስድስት ሚሊየን ስምንት መቶ ስድሳ አራት ሺህ ስምንት መቶ አንድ) በማከል በአጠቃላይ ብር 620,187,557 (ስድስት መቶ ሃያ ሚሊየን አንድ መቶ ሰማንያ ሰባት ሺህ አምስት መቶ ሃምሳ ሰባት) መሰብሰብ ችሏል፡፡ በበጀት ዓመቱ ከታክስ በፊት 333 ሚሊየን ብር ትርፍ ያስመዘገበ ሲሆን ለዚህ ዉጤት መመዝገብ የአዳዲስ መንገዶች መጨመር፤ የትራፊክ ፍሰቱ ማደግ ፤ የኢንተርፕራይዙ ሰራተኞች ትጋት እና ብረታት እንዲሁም የአመራሩና የባላድርሻ አካላት አስተዋፅዖ ድምር ዉጤት በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባም ተገልጿል፡፡

በበጀት ዓመቱ ከተከናወኑ አበይት ተግባራት አንዱ በ6.3 ቢሊየን ብር ወጪ የተገነባው እና 92 ኪ.ሜ ርዝመት ያለው ለኢንተርፕራይዙ  3ኛ የሆነው የሞጆ- ባቱ የክፍያ መንገድ ከመስከረም 10/2014 ዓ.ም ጀምሮ ለአገልግሎት ክፍት ማድረግ ይገኝበታል፡፡

የሞጆ- ባቱ  የክፍያ መንገድ የአፍሪካ ትራንስ ሀይዌይ አካል የሆነው የአዲስ አበባ- አዳማ- ሞያሌ- ናይሮቢ- ሞምባሳ የመንገድ ኮሪደር ነዉ፤ መንገዱ ለአካባቢው ህብረተሰብ የስራ ዕድል መፍጠሩ፤ በከተሞች መካከል ቅርበት በመፍጠር የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ማጠናከሩ፤ የጉዞ ሰዓትን መቀነሱ፤ የጥገና ወጪን መቀነሱ መንገዱ የሚያስገኛቸው ጠቀሜታዎች በመሆናቸው ይህን የሀገር ሀብት የሆነውን መንገድ መንከባከብ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

የሞጆ – ባቱን 92 ኪ.ሜ የክፍያ መንገድ ስራ ለማስጀመር ከአስተዳደራዊ ስራዎች ባሻገር የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደቱን ቀልጣፋና ደህንነቱ የተጠበቀ ለማድረግ ከህብረተሰቡ ጋር እንዲሁም ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር በኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ፋይዳ ዙሪያ እንዲሁም በአገልግሎት አሰጣጥና በመንገድ ደህንነት ዙሪያ ያለውን አሰራር በሚመለከት ሰፊ ውይቶች ተደርገዋል፡፡

የክፍያ መንገዶችን ደህንነት ከማስጠበቅ አኳያ በተለያዩ ቦታዎች ሰፊ የግንዛቤ መፍጠሪያ መርሃ ግብሮችን በማዘጋጀት፤ በማስተማር እና በመንገዱ ክልል ውስጥ የ24 ሰዓት የመንገድ ላይ ቅኝታዊ ቁጥጥር በማድረግ እንዲሁም ከባለድርሻ አካላት በተለይም ከጸጥታ አካላት  ጋር በቅንጅት ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ከትራፊክ ደህንንት አንጻርም አደጋ በሚያጋጥም ጊዜም የአደጋ መቆጣጠሪያ እና የጉዳት መቀነሻ መለኪያዎች መሰረት በብቃት በመፈጸም፤ ለአደጋ ምላሽ ሰጪነት በማሳደግ፤ በደረሰ አደጋ የተዘጉ የመንገድ ክፍሎችን በፍጥነት ክፍት በማድረግ የትራፊክ ፍሰቱ ሳይሰተጓጉል እንዲቀጥል ማድረግ መቻሉ፡፡

በተጨማሪም የጥገና ቁሳቁሶች እንዲሟሉና የባለሙያ ልምድና አቅምን በማሳደግ በውስጥ አቅም በአሰቸኳይ በአገልግሎት እድሜ ምክንያት በመንገዱ እና በመንገድ ሀብቶች የደረሱትን አደጋዎች በመጠገን የመንገዱ ምቾት እና ደህንነት እንዳይጓደል ተሰርቷል፡፡

የ24/7 የክፍያ መንገድ አገልግሎት ሳይስተጓጎል የሰራተኞች እና የመንገድ ተጠቃሚዎችን ደህንነት ባስጠበቀ ሁኔታ ማስቀጠል መቻሉ በጠንካራ ጎን የታየ ሲሆን፤ አልፎ አልፎ ኃላፊነት በማይሰማቸዉ እና በሀገር ሀብት ላይ ስርቆት የመፈፀም እኩይ ተግባሮች ላይ በተሰማሩ ግለሰቦች የመንገዱ ንብረቶች በተለይ የአጥር ስርቆት ከመኖሩ ጋር ተያይዞ በመንገዱ ክልል ዉስጥ የሚገቡ አንስሳት መኖራቸው ፤ ከጂቡቲ የሚነሱ የድሬደዋ- ደወሌ የክፍያ መንገድ  ተጠቃሚ የተሽከርካሪዎች የክብደት ቁጥጥር ስራ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መሆናቸው ተገልጿል፡፡

የታዩ ደካማ ጎኖችን በጥልቀት በመመርመርና ማስተካከያ በማድረግ፤ የነበሩ ጠንካራ ጎኖችን በማዳበር ከዚህ በተሻለ መልኩ ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀስ የኢንተፕራይዙን ተልዕኮ ከግብ ለማድረስ በ2015 ዓም ከመንገዱ ተጠቃሚዎች የሚሰበሰብ ገቢ ወቅታዊ የጥገና እና አስተዳደራዊ ወጪዎችን ሸፍኖ ትርፋማ ሆኖ እንዲዘልቅ ለማድረግ የሚያስችል የክፍያ ታሪፍ ክለሳን እና የመንገዱን አገልግሎት ይበልጥ ለማዘመን የኤሌክትሮኒክ ክፍያ ስርዓት ዝርጋታን ጨምሮ በርካታ ስራዎችን ለመከናወን መታቀዱ ተገልጿል፡፡