የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝኤክስፕረስ ማይልስበሚል መጠሪያ ለደህንነት አምባሳደሮች ዕውቅና መስጠቱን ገለጸ።

የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ “ኤክስፕረስ ማይልስ” አዋርድ (ExpressMiles Award) በሚል መጠሪያ ለደህንነት አምባሳደሮች ዕውቅና እና ሽልማት ሰጥቷል።

የኢንተርፕራይዙ ኃላፊዎችና ሰራተኞች፤ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፤እንዲሁም ተሸላሚዎች የተገኙ ሲሆን የዕውቅና ፕሮግራሙ መዘጋጀቱ የመንገድ ደህንነትን ከማረጋገጥ አኳያ አዎንታዊ ሚና እንዳለው ጸገልጸዋል።

በዕለቱ ሽልማቱን ያበረከቱት የኢንተርፕራይዙ የፋይናንስ አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ አስራት ‹‹የዕውቅና እና የሽልማት ፕሮግራሙ በዋናነት ጥፋተኛ አሽከርካሪዎችን መውቀስ እና ተጠያቂ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ህግ እና ደንብ አክብረው የሚጓዙ አሽከርካሪዎችን የማመስገን ልምድ እንዲዳብር ለማድረግ እንዲሁም ሌሎች አሽከርካሪዎችን ለማበረታታት ያለመ ነው፡፡›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

አሽከርካሪዎች ምንም አይነት አደጋ አለማድረሳቸው፤ በፍጥነት መንገዱ ብዙ ምልልስ ማድረጋቸው እንዲሁም በመልካም ስነ ምግባር ማሽከርከራቸው የሽልማቱ መስፈርት መሆኑም ተገልጻል፡፡  እውቅናው ከአሽከርካሪዎች ባለፈ የንብረት ባለቤቶችንም የሚያበረታታ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል በማለት የመንገድ ደህንነትን ለማስጠበቅና የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የድርሻቸውን እንደሚወጡም ገልጸዋል፡፡