የትራፊክ አደጋ

የትራፊክ አደጋ

ሃገራችን እያስመዘገበች ለምትገኘው ኢኮኖሚያዊ ፣ማህበራዊና ፖለቲካዊ እድገት የትራንስፖርት ዘርፍ እያበረከተ ያለው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ ዘርፉ እያበረከተ የሚገኘው ጠቀሜታ ከፍተኛ እንደመሆኑ መጠን በአግባቡና ወቅቱ በሚጠይቀው የአሰራር ስርዓት ታግዞ ካልተሰራ የሚያስከትለው ችግር ከፍተኛ ነው፡፡

ከችግሮቹ ውስጥም የመንገድ የትራፊክ አደጋ ጉዳይ አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የትራፊክ አደጋን በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃንና በማህበራዊ ድህረ ገፆች ላይ መስማትና መለቀቅ የተለመደ ክስተት እየሆነ መጥቷል ፡፡ በተለያየ ወቅትና ጊዜያት ታላላቅ የዓለምና የአፍሪካ ምሁራን እንዲሁም ታዋቂ ሰዎች የትራፊክ አደጋ ሰለባ ሆነዋል ፡፡ አደጋው የሰው ህይወትና አካል ከመቅጠፍ ባሻገር በንብረት ላይ እያስከተለው ያለው ጉዳት ከፍተኛ ነው፡፡

የትራፊክ አደጋ ጎልቶ የሚታየው በአፍሪካ አህጉር ሲሆን በታዳጊ ሀገራት ላይ  የአደጋው መጠን ከእለት ወደ እለት እያሻቀበ መጥቷል ፡፡ ከነዚህም የትራፊክ አደጋ ከሚስተዋልባቸው መካከል የምስራቅ አፍሪካዋ ሀገር ኢትዮጵያ ትገኛለች ፡፡ ከግማሽ ሚሊየን የማይበልጥ ተሸከርካሪዎች ባሉባት ሀገር በተለያዩ ጊዜያትና በተለያዩ ቦታዎች እጅግ ከፍተኛ የትራፊክ አደጋዎች እየተከሰቱ ይገኛሉ፡፡ ይህም ሁኔታ በሃገራዊ የእድገት ግስጋሴ ላይ የራሱ የሆነ አሉታዊ አሻራ ማሳረፉ አልቀረም ፡፡በተለያዩ አካባቢዎች ላይ የሚከሰተው የመንገድ ትራፊክ አደጋ ሃገሪቱን በልማት ጎዳና ወደ ፊት ሊያራምዷት የሚችሉ በርካታ ሰዎችን እያሳጣ ይገኛል፡፡ ለስራ ይተጉ የነበሩ እጆች እና እግሮች በአደጋው ምክንያት ወደ ጠባቂነት ተቀይረዋል፡፡ከዚህም ባሻገር እያስከተለ ያለው ኢኮኖሚያዊና  ማህበራዊ ችግር ብሎም ስነ-ልቦናዊ ጉዳቱ እየገዘፈ መጥቷል ፡፡የትራፊክ አደጋን  ለመከላከል መንግስት የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ቢገኝም ውጤቱ ግን የሚፈለገው ደረጃ ላይ አልደረሰም ፡፡ አደጋውን ለመከላከልና የመንገድ ትራፊክ ደህንነትን ለማረጋገጥ ብሎም ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት በሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት መታገዝ ይኖርበታል ፡፡

ከዚህም ባሻገር መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት ከትምህርት ቤት እስከ ታችኛው ማህበረሰብ ድረስ ዘልቆ በመግባት ስለችግሩ አሳሳቢነት  ወጥነት ያላቸው መርሃ ግብሮችን ነድፎ የዘመቻ ስራዎችን በተጠናና ውጤታማ በሆነ መልኩ መስራት በጣም አስፈላጊ ነው፡፡

የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ከዋና ዋና ግቦች መካከል  አንዱና ዋነኛው የመንገደኞችን ደህንነት መጠበቅ ነው ፡፡ይህን  የመንገደኞች ደህንነት በዘላቂነት ለማስቀጠልና የሚደርሱ የትራፊክ አደጋዎችን በመቀነስ በሰው እና በንብረት ላይ አደጋዎች እንዳይከሰቱእና  ከተከሰቱም በኋላ ሶስት ዋና ዋና ተግባራትን እያከናወነይገኛል፡፡ ፡፡እነዚህም የቅድመ መከላከል፣አደጋን መቆጣጠር እና ድህረ አደጋ አስተዳደር በዋነኛነት እየተሰሩ ናቸው ፡፡የክፍያ መንገድ ለሃገራችን አዲስ እንደመሆኑ መጠን ኢንተርፕራይዙ ከተለያዩ ባለድርሻ ተባባሪ አካላት ጋር አደጋውን ለመቀነስ እንደ ሃገር እና  በተቋም ደረጃም  መስራት የተቻለ ሲሆን ከኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን የመንገዱን ደህንነት እንዲሁም የትራፊክ ህጎችን በማስጠበቅ፣ከኦሮሚያ ትራንስፖርት ኤጀንሲ በመንገድ ደህንነት ዙሪያ ስልጠና ለአሽከርካሪዎች በቪዲዮ ኮንፍረስ በመስጠት በጋራ ለመንቀሳቀስ በርካታ  ጥረቶች ተደርገዋል ፡፡

የትራፊክ አደጋ በአዲስ አበባ አዳማ የፍጥነት መንገድ ላይ የሚከሰተው የአሽከርካሪዎች ግንዛቤ ዝቅተኛ በመሆኑ ምክንያት ሲሆን በኢንተርፕራዙ ይህን ክፍተት ለመሙላት የአጭርና የረጅም ጊዜ እቅድ በመንደፍ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እየሰራ ይገኛል ፡፡ከእነዚህም የግንዛቤ ማስጨበጫዎች መካከል የአሽከርካሪዎችን ደህንነት ሊያስጠብቁ የሚችሉ የህትመት ውጤቶችን በማሰራጨት፣ የድምፅ መልዕክቶችን በክፍያ ጣቢያዎች በማስተላለፍ እና የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃንን  በመጠቀም ብሎም የደህንነት ሳምንት/Safety campaign/ በማዘጋጀት ለውጦች ለማምጣት ተችሏል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ያሉትን ቴክኖሎጂዎች በመጠቀምና የመንገድ ቁጥጥርን በማሻሻል በመስራት ላይ ነው፡