================================
ኢክመኢ[ETRE ሐምሌ 30/2018 ዓ/ም]
የኢትዮጵያ ክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን በተግባር ለመወጣት በሚያደርጋቸው ተከታታይ ክንውኖች አንዱ የሆነውን ተግባር ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል የደም ባንክ ጋር በትብብር “በሚተካ ደም የማይተካውን የሰው ሕይወት እንታደግ” በሚል መሪ ቃል ያዘጋጀውን የ2018 ዓ.ም. የክረምት በጎ ፈቃድ የደም ልገሳ መርሃ ግብር በተሳካ ሁኔታ አካሂዷል።
በዚሁ መርሃ ግብር የኢንተርፕራይዙ ከዋና መሥሪያ ቤትና ከቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶች የተውጣጡ ሠራተኞችና አመራሮች በራስ ተነሳሽነት፣ በሙሉ ፈቃዳቸው እና በከፍተኛ የሰብዓዊነት ስሜት በመሳተፍ ደም ለግሰዋል። ይህ የበጎ ፈቃድ ተሳትፎ የኢንተርፕራይዙ ሠራተኞች ለማኅበረሰቡ ሕይወት ያላቸውን ኃላፊነት፣ የመረዳዳት ባህል እና ሰብዓዊ እሴቶችን በተግባር ያሳየ ተግባር ሆኗል።
በመርሃ ግብሩ መክፈቻ ላይ የሰው ሀብት ሥራ አመራር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ዘርፌ ሙሉጌታ ባደረጉት ንግግር፣ የዘንድሮው የበጎ ፈቃድ የደም ልገሳ መርሃ ግብር ሰብዓዊነትን፣ መረዳዳትን እና ማኅበራዊ ኃላፊነትን በተግባር የሚያንጸባርቅ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል። በተጨማሪም ደም ለመለገስ በፈቃደኝነት ለተሳተፉ አመራሮችና ሠራተኞች፣ እንዲሁም መርሃ ግብሩን በማስተባበር ላይ ለተሳተፉ ሁሉ በኢንተርፕራይዙ ስም ልባዊ ምስጋና አቅርበዋል።
መርሃ ግብሩ በሠራተኞች መካከል የበጎ ፈቃደኝነትን፣ የመረዳዳትን እና የሰብዓዊነትን እሴቶች ይበልጥ ያጠናከረ ሲሆን፣ ኢንተርፕራይዙም ከዋና የሥራ ተልዕኮው ባሻገር ለማኅበረሰቡ ጤናና ደኅንነት ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር ያረጋገጠበት ተግባር መሆኑ ተጠቅሷል።
የኢትዮጵያ ክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ዘመናዊና ቀልጣፋ የክፍያ መንገድ አገልግሎትን ከማቅረብ ባሻገር፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በአካባቢ ጥበቃ እና በሌሎች ማኅበራዊ ተግባራት በንቃት በመሳተፍ ለአገርና ለማኅበረሰብ የሚያበረክተውን አስተዋፅኦ በቀጣይነት እያጠናከረ መሆኑንም አስታውቋል።
በመርሃ ግብሩ ማጠቃለያ ላይ የኢንተርፕራይዙ አመራሮች ለደም ለገሱ ሠራተኞችና በጎ ፈቃደኞች፣ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ቀይ መስቀል የደም ባንክ ለተደረገው ውጤታማ ትብብር ከፍተኛ ምስጋና አቅርበው፣ መሰል ሕይወት አድን መርሃ ግብሮች ወደፊትም በመደበኛነት እንደሚካሄዱ ገልጸዋል።
“አንድ የደም ልገሳ ብዙ ሕይወቶችን ሊያድን ይችላል፤ የዛሬው በጎ ተግባር የነገውን ተስፋ ያበራል።”
የኢትዮጵያ ክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ
“ደኅንነትዎ የክብር ስማችን ነው!!”

