የኢ.ክ.መ.ኢ መንገዱን ውብና ምቹ ለማድረግ በአረንጓዴ ልማት እና አካባቢ ጥበቃ

የኢ.ክ.መ.ኢ መንገዱን ውብና ምቹ ለማድረግ በአረንጓዴ ልማት እና አካባቢ ጥበቃ

የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ መንገዱን ውብና ምቹ ለማድረግ በአረንጓዴ ልማት እና አካባቢ ጥበቃ ረገድ በርካታ ስራዎችን እያከናወነ ቢሆንም መንገድ ላይ የሚጣሉ ቆሻሻዎች ለስራው እንቅፋት መሆናቸውን ገለፀ፡፡

ኢንተርፕራይዙ በተያዘው በጀት አመት ስምንት ወራት የፍጥነት መንገዱን ውብ እና ምቹ ለማድረግ ብሎም በምሽት ከተቃራኒ አቅጣጫ የሚመጡ የተሽከርካሪ መብራት ጨረር ለመከላከል እንዲያግዝ በአጠቃላይ 70727 ችግኞች በመንገዱ መሀልና ዳርቻ በመትከል እየተንከባከበ እንዲሁም 76 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውን የመንገዱን ክልል በዘመናዊ የጽዳት መኪና ታግዞ በማፅዳት ለመንገዱ ተጠቃሚዎች ምቾት እና ደህንነት እየሰራ ይገኛል፡፡

የኢንተርፕራይዙ የአካባቢ ጥበቃ ዘርፍ በአደጋ አማካኝነት የተጎዱ ችግኞችን የጉዳታቸውን አይነት በመለየት ፤ መተካት ያለባቸውን እና የቦታውን የአየር ንብረት የሚቋቋሙ የችግኝ አይነቶችን ለይቶ የመተካት ስራ በየግዜው እያከናወነ ይገኛል፡፡

ለመንገዱ አረንጓዴነት ችግኞችን ለመትከልና ፤ አደጋን ጨምሮ በተለያየ ምክንያት የተጎዱትን ለመተካት እንዲያስችል እንዲሁም ለችግኝ አቅርቦት የሚወጣውን ወጪ ለመቀነስ በኢንተርፕራይዙ የራሱን የችግኝ ጣቢያ በማቋቋም በአይነት 8 በቁጥር 16461 ያህል የችግኝ ዘሮችን ለማፍላት ተችሏል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ኢንተርፕራይዙ በ2010ዓ.ም ከደን እና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር  ጋር በመተባበር በመንገዱ ዳርና ዳር ለሚተከሉ የዛፍ ችግኞች የአየር ንብረት ሁኔታ ፣ ከፍታ ፣ የአፈር አይነት ፣በአከባቢው የሚገኙ የውጪ እና አገር በቀል ዛፎች የሚተከሉባቸውን ቦታችና የዛፍ ችግኝ አይነቶች ላይ በጋራ ጥናት በማካሄድ 19750 ያህል ችግኞችን የመትከል ስራ ተሰርቷል፡፡

ኢንተርፕራይዙ በመንገድ ላይ ለሚጣሉ ቆሻሻዎች በየማረፊያ ቦታዎች ላይ 30 የቆሻሻ መጣያዎችን ቢያስቀምጥም ከተዘጋጀው መጣያ ውጭ በመጣል እንዲሁም ከሌሎች ቦታዎች በመኪና ጭነው ቆሻሻዎችን በመንገዱ ክልል ውስጥ በመዘርገፍ የመንገዱን ውበት በከፍተኛ ደረጃ እያጠፉት ይገኛሉ፡፡

በመሆኑም ህብረተሰቡ በተለይም የመንገዱ ተጠቃሚ ደንበኞች ለመንገዱ ፅትና ውበት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ኢንተርፕራይዙ ጥሪውን ያቀርባል፡፡