ደህንነት

ደህንነት

ደህንነት

በሀገራችን የገቢና ወጪ እቃዎች ዝዉውር 95% እንዲሁም ለተለያዩ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ክንውኖች ከሚደረገው የመንገደኞች እንቅስቃሴ 90% ያህሉ አገልግሎት የሚያገኘው በመንገድ ትራንስፖርት አማካይነት ነው፡፡ በመሆኑም ይህ ዘርፍ ለሀገር ልማትና እድገት የጀርባ አጥንት በመሆን እያበረከተ ካለው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አስተዋፅዖ አንጻር ዘርፉ በተገቢና በተጠናከረ እንዲሁም በተቀናጀ ሁኔታ ካልተመራ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ሊያመዝን እንደሚችል አያጠራጥርም፡፡

በዓለም አቀፍ የመንገድ ትራፊክ አደጋ መመዘኛ መለኪያ ሆኖ እየተሰራበት ባለው በ10,000 ተሽከርካሪዎች የሞት አደጋ ሲሰላ በሀገራችን በ2008 በጀት ዓመት 61.4 የሰው ሞት ሲደርስ ይህ አሃዝ በ2009 ዓ.ም መንግስት ባለው አቅም ስራዎች በመስራቱ የሞት መጠን ወደ 54 ዝቅ ማድረግ ተችሏል፡፡ በመንገድ ትራፊክ አደጋ መከላከል ዙሪያ ከፍተኛ ስራ በሰሩ ሀገሮች ይህ አሀዝ ከ10 በታች ሲሆን በአፍሪካም ከ30 በታች ይመዘገባል፡፡ ከዚህ አንፃር ሀገራችን በመንገድ ትራፊክ አደጋ ከፍተኛውን ደረጃ እንድትይዝ አድርጓታል፡፡

ሀገራችን በዚህ ችግር ውስጥ የምትገኝ በመሆኗ ምክንያት አደጋውን ለመቀነስ እንዲቻል በ2003 ዓ.ም ሀገራዊ የትራፊክ ንቅናቄ ተጀምሯል፡፡ በወቅቱም ጉዳዩ በቀጥታና በተዘዋዋሪ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት እንዲሳተፉ ተደርጐ የተለያዩ ተግባሮች ተከናውነዋል፡፡በመንግስት ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው በመሆኑ የተጀመረው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለማድረግ የሚሠራ መሆኑን በመንግስት በኩል አቋም ተይዟል፡፡ የዚህ ንቅናቄ አንዱ አካል የሆነዉ የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ በአዲስ አበባ – አዳማ የፍጥነት መንገድ ለተገልጋዮች ክፍት ተደርጎ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ጀምሮ በትራፊክ አደጋ በርካታ ስራዎች መስራት ተችሏል፡፡

የመንገዱ ደህንነትንና ምቾት መጠበቅ ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ሕይወት እስከ ሞት ሊያደርሱ የሚችሉ የትራፊክ አደጋዎችን መንስዔና ምክንያቶች በመለየት፣ ቅድመ-መከላከልን ከፍ በማድረግና አደጋ በሚያጋጥም ጊዜም ፈጣን እርዳታዎችን በማድረግ ሊያደርሱ የሚችሉትን ጉዳት መቀነስ የሚያስችሉ በርካታ ስራዎች በኢንተርፕራይዙ የመንገድ እና ትራፊክ ደህንነት አስተዳደር ቡድን እና የኢንተርፕራይዙ ትራፊክ ፖሊሶች በጋራ የተሰራ ቢሆንም የሚደርሱ የትራፊክ አደጋዎችን እና በሰዉ ላይ የሚደርሱ ሞት እና አካላዊ ጉዳት መቀነስ አልተቻለም፡፡ በተለይ በመንገድ ደህንነት ስራ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎችን የመፈጸም አቅም ለማጎልበት እንዲሁም ለሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት የግንዛቤ ማስፋት ስራዎች ተሰርተዋል፡፡

በአዲስ አበባ አዳማ የፍጥነት መንገድ ላይ ለትራፊክ አደጋ በምክንያትነት ከሚጠቀሱት ውስጥ ከፍጥነት በላይ ማሽከርከር፣ ቸልተኝነት፣ የተሽከርካሪዎች የቴክኒክ ጉድለት፣ ከክብደት በላይ ጭኖ ማሽከርከር፣ በድካም ስሜት ውስጥ ሆኖ ማሽከርከር እንዲሁም አልኮልና የተለያዩ ዕፆችን ተጠቅሞ ማሽከርከር ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

ስለሆነም በፍጥነት መንገዱ ላይ እየተስተዋለ ካለው የትራፊክ ፍሰት መጨመር ጎን ለጎን የመንገድ ደህንነትን ከማረጋገጥ ረገድ ሰፊ ስራ መሰራት አለበት፡፡ የግንዛቤ ማስያዝ ስራዎችን በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ መስራት፤ የመንገድ ላይ ቁጥጥርን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ እንዲሆን ማድረግ፤ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር መስራት ይገባል፡፡