በአዲስ- አዳማ የፍጥነት መንገድ ላይ #የተዘረፉ ሶስት ተሽከርካሪዎች መገኘታቸው ተገለጸ፡፡

በአዲስ- አዳማ የፍጥነት መንገድ ላይ #የተዘረፉ ሶስት ተሽከርካሪዎች  መገኘታቸው ተገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ከሚያስተዳድራቸው የፍጥነት መንገዶች አንዱ የሆነው እና አገልግሎት መስጠት ከጀመረ አምስት ዓመት ከስምንት ወር በላይ የሆነው የአዲስ- አዳማ የፍጥነት መንገድ ያልተቋረጠ የ24/7 የክፍያ መንገድ አገልግሎት እየሰጠ ነው፡፡

ደህንነቱ የተጠበቀ፤ ምቾቱ የተረጋገጠ እንዲሁም ዘመናዊ እና አስተማማኝ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው ተቋሙ በተለያዩ ጊዜ የሚገጥሙትን ተግዳሮቶች በማለፍ ስኬታማ ጉዞ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

ካለፈው ዓመት ጀምሮ በመንገዱ ላይ በተለያየ ጊዜ የጸጥታ ስጋቶች እና የስርቆት ወንጀሎች ሲፈፀሙና ክትትል ሲደረግባቸው የቆየ ቢሆንም በተለይ ባለፉት ሶስት ወራት የታየው የተሽከርካሪ ስርቆት በመንገዱ ደህንነት ላይ ከፍተኛ ስጋት ፈጥሮ ቆይቷል፡፡

የተለያየ የጉዳት መጠን የተስተዋለበት ዝርፊያ አሽከርካሪዎች በየሶስት ኪ.ሜ በሚገኙ ሌይ ባይ የተሰኙ የማረፊያ ቦታዎች ለማረፍ እና የተሽከርካሪዎቻቸውን የቴክኒክ ሁኔታ ለማየት በሚቆሙበት ጊዜ የሚፈፀም ሲሆን የተለያዩ  አይነት ጌጣጌጦች፣ ሞባይሎች፣ የብር ኖቶች፣ እንዲሁም በተሽከርካሪ ላይ የተጫኑ ንብረቶች የዝርፊያው ሰለባ ሆነዋል፡፡

ዘራፊዎቹ አብዛኛውን ጊዜ በኢንተርፕራይዙ የሚደረገውን የፓትሮል ቁጥጥር ሰዓት በመለየት እና ፓትሮል ተሽከርካሪዎች ማለፋቸውን በማረጋገጥ እንዲሁም ጨለማን ተገን አድርገው ዱላ፣ ጩቤ፣ ገጀራ፣ እንዲሁም የነፍስ ወከፍ መሳሪያ በመጠቀም የሚፈጽሙ ናቸው፡፡

እነዚህ የተደራጁ ዘራፊዎች በመሳሪያ በመታገዝ መንገደኞችን በማስፈራራት የያዙትን ንብረት በመውሰድና ተሸከርካሪው ላይ ያሉ ንብረቶችን በመዝረፍ የቆዩ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ሙሉ ተሸከርካሪውን በመዝረፍ ሲሰወሩ ቆይተዋል፡፡ በዚህም በሎሜ ወረዳ ወይም በመንገዱ አጠራር ከኪ.ሜ 49 እስከ 53 ባለው የመንገዱ ክፍል ላይ በተለምዶ ኤፍ ኤስ አር የተሰኙ ተሸከርካሪዎች ላይ የተፈፀሙት ሶስት የተሸከርካሪ ዝርፊያዎች ግን ከፍተኛ ሆነው ተመዝግበዋል፡፡

ንብረቶቹን የሰረቁና የዘረፉ እንዲሁም የሚያሻሽጡ ደላሎች፤ ተሸከርካሪዎቹን የሚፈታቱ እና የሚያሸሹ መካኒኮች፤ መኖራቸው የተደረሰበት ሲሆን የተሰረቁ ንብረቶችን የሚያከማቹበት መጋዘን እንዲሁም 3ቱም የተዘረፉ ተሸከርካሪዎች በደረሰ ጥቆማ መሰረት በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡

ዝርፊያዎችን ተከታትሎ ለመያዝ ከማህበረሰቡ ጋር የተደረጉ ውይይቶች በመንገዱ ዙሪያ ካሉ የከተማ አስተዳር የጸጥታ ዘርፎች ጋር የተሰሩ ስራዎች ያደረጉት አስተዋፅኦ እንዳለ ሆኖ በተለይ የተሽርካሪዎችን ስርቆት ተከታትለው በቁጥጥር ስር ያዋሉት የምስራቅ ሸዋ ዞንና ሎሜ ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት  ከኢንተርፕራይዙ ፀጥታ ዘርፍ ጋር በመቀናጀት መሆኑ ተገልጿል፡፡

የሚደርሱ ጥቆማዎችን መሰረት በማድረግም በተደረገ ክትትል 15 ተጠርጣሪዎችን፣ በፍጥነት መንገዱ ላይ እንዲሁም ከሌላ ቦታ የተሰረቁ አብዛኛውን ንብረቶች እና ለዝርፊያ የሚጠቀሙባቸውን ቁሳቁሶች  በኤግዚቢትነት መያዝ መቻሉን የምስራቅ ሸዋ ዞን የሎሜ ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት አስታውቋል፡፡

 

በቀጣይም ኢንተርፕራይዙ ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ከግብረ አበሮች ባለፈ ዝርፊያውን የሚመራው አካል እስኪገኝ ድረስ ክትትሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል እያሳወቀ የተሸርካሪ ባለንብረቶች  የስራ ኃላፊነት የሚሰጧቸውን አሽከርካሪዎች በሚገባ ማወቅና አስፈላጊ መረጃ መያዝ እንዳለባቸው እያስታወሰ አሁን ለተገኘው ውጤት ህብረተሰቡ እና የፀጥታ አካላት ላደረጉት ርብርብ ምስጋናውን ያቀርባል ፡፡

 

የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ

 

ደህንነትዎ የክብር ስማችን ነው!