የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ በ2012 በጀት ዓመት ከሶስት መቶ ሰማኒያ አንድ ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ሰበሰበ፡፡

የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ በ2012 በጀት ዓመት ከሶስት መቶ ሰማኒያ አንድ ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ሰበሰበ፡፡

የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ በተያዘው የበጀት ዓመት አስር ስትራቴጂካዊ ግቦች እንዲሁም ዘጠኝ የማስፈጸሚያ ፕሮጀክቶችን ነድፎ ሲተገብር ቆይቷል፡፡ ዕቅዱንም እስከ ፈጻሚ ድረስ በማውረድ መተግበር ተችሏል፡፡
በበጀት ዓመቱ በአዲስ- አዳማ እና በድሬዳዋ- ደወሌ የክፍያ መንገዶች በድምሩ 8,677,222 (89.39%) የትራፊክ ፍሰት በማስተናገድ ከክፍያ መንገድ አገልግሎት ብር 350,723,030 (ሶስት መቶ ሃምሳ ሚሊየን ሰባት መቶ ሃያ ሶስት ሺህ ሰላሳ) ተሰብስቧል፡፡ የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ መጠነኛ ተፅዕኖ በማሳደሩም አፈፃፀሙ 86.56% ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ በተጨማሪም ከልዩ ልዩ ገቢዎች (ከማስታወቂያ ቦታዎች ኪራይ፣ ከወደሙ የመንገድ ሃብቶች ካሳ ክፍያ፣ ከተሽከርካሪ ማንሻና መጎተቻ…) ብር 31,169,629 (ሰላሳ አንድ ሚሊየን አንድ መቶ ስልሳ ዘጠኝ ሺህ ስድስት መቶ ሃያ ዘጠኝ) በማከል በአጠቃላይ ብር 381,892,659 (ሶስት መቶ ሰማኒያ አንድ ሚሊየን ስምንት መቶ ዘጠና ሁለት ሺህ ስድስት መቶ ሃምሳ ዘጠኝ) መሰብሰብ ተችሏል፡፡
ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም አገልግሎት አየሰጠ የሚገኘው ተቋሙ የላቀ አፈፃፀም ለማስመዝገብ የተፈጠሩ መልካም አጋጣሚዎችን ተጠቅሞ ያሉትን ጠንካራ ጎኖች አጠናክሮ በማስቀጠል፤ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በመቋቋም፤ የሚስተዋሉ ድክመቶችን በመቅረፍ፤ ያለውን የሰው ኃይል በዕውቀትና በክህሎት በማሳደግ፤ የአሰራር ስልቶችን በማሻሻል በስፋት ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡
የመንገዱን ደህንነት ከማስጠበቅ አኳያ በተለያዩ ቦታዎች ሰፊ የግንዛቤ መፍጠሪያ መርሃ ግብሮችን በማዘጋጀት፤ በማስተማር እና በመንገዱ ክልል ውስጥ የ24 ሰዓት የመንገድ ላይ ቅኝታዊ ቁጥጥር በማድረግ እንዲሁም ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ሲሰራ ቆይቷል፡፡ በዚህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በትራፊክ አደጋ በአዲስ- አዳማ የፍጥነት መንገድ የደረሰ ሞትን ከ50% በላይ መቀነስ ተችሏል፡፡ አምና በተመሳሳይ ወቅት በደረሰ የትራፊክ አደጋ 25 ሞት ያጋጠመ ሲሆን ዘንድሮ 11 ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
በተጨማሪም የጥገና አቅምን በማሳደግ የጥራት ዋስትና ውሉን በመጠቀም 100 ሌን- ኪ.ሜ አስፋልት እንዲሁም በውስጥ አቅም 1.8 ኪ.ሜ የመንገድ አካፋይ ብረት (Gard rail) ጥገና በአዲስ- አዳማ የፍጥነት መንገድ ላይ ተከናውኗል፡፡ በአገልግሎት እድሜ ማብቃት እና በአደጋ ምክንያት በመንገድ ንብረቶች ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን በመጠገን የመንገዱ ምቾት እና ደህንነት እንዳይጓደል ተሰርቷል፡፡


የማህበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አኳያ በቢሾፍቱ እና ዱከም አካባቢ ከ336 ሺህ በላይ በሆነ ወጪ 160 የሚሆኑ አባወራዎችን ንፁህ የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ተችሏል፡፡ በድሬዳዋ- ደወሌ የክፍያ መንገድ አካባቢ አይሻ ወረዳ ከ316 ሺህ በላይ ወጪ በማድረግ የህዝብ ትምህርት ቤት ጥገና ድጋፍ ተደርጓል፡፡
የአገልግሎት አሰጣጡን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳደገ የሚገኘው የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው፡፡ የዋና መስሪያ ቤቱን የስራ ቦታን ምቹ የማድረግ (Ergonomics) ስራ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ሰራተኞች በተሻለ የስራ አካባቢ ስራቸውን እንዲያከናውኑ ተደርገዋል፡፡ የመረጃ ቋት አቅም ማሳደግ፤ የሃብት መረጃ አስተዳደር ስርዓት (ERP) ትግበራ፤ የመንገድ ላይ መብራት ማስፋፊያ ዝርጋታ ፕሮጀክቶች ተከናውነዋል፡፡
ኢንተርፕራይዙ በአዲስ አበባ- አዳማ እና ድሬዳዋ- ደወሌ የክፍያ መንገዶች የ24/7 የክፍያ መንገድ አገልግሎት መስጠቱ፤ በኢንተርፕራይዙ የመንገድ አካፋይ ላይ የሚገኙ ንብረቶች በወቅቱ መጠገኑ፤ 35 ሺህ ችግኞችን በመትከል እና ከ85% በላይ የሚሆኑትን ማጽደቅ መቻሉ፤ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል የተደረገ ቅድመ ዝግጅት እና ግብአት በወቅቱ በማቅረብ ከፍተኛ ርብርብ መደረጉ፤ የፕሮጀክቶች አፈጻጸም መሻሻል የታየበት መሆኑ በጠንካራ ጎኑ ተገምግሟል፡፡

በድሬደዋ- ደወሌ መንገድ ላይ ያለው የክብደት ቁጥጥር ውጤታማነት አስተማማኝ አለመሆኑ እና ከክብደት በላይ ጭነው የሚጓዙ ተሽከርካሪዎች በመንገዱ ላይ ጉዳት እያደረሱ መሆኑ ትኩረት የሚሻ ጉዳዮች መሆናቸው ተገልጿል፡፡

የ2012 በጀት ዓመት የውጤት ተኮር ስርዓት ዕቅድ አፈፃፀም አጠቃላይ ውጤት 86.37% ሲሆን የአፈፃፀም ደረጃውም ከፍተኛ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ በቀጣይም የታዩ ደካማ ጎኖችን በጥልቀት በመመርመርና ማስተካከያ በማድረግ፤ የነበሩ ጠንካራ ጎኖችን በማዳበር የሞጆ- ሐዋሳ የፍጥነት መንገድን ተረክቦ ስራ ማስጀመር እንዲሁም የአዲስ- አዳማ የፍጥነት መንገድ አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎችን ገንብቶ አገልግሎት ማስጀመርን ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀስ የኢንተፕራይዙን ውጤታማነት ከፍ ማድረግ እንደሚገባ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

 

በኢ.ክ.መ.ኢ ኮሙዩኒኬሽንና ማርኬቲንግ ቡድን የተዘጋጀ
ደህንነትዎ የክብር ስማችን ነው!