#ምክንያት_አልሆንም

#ምክንያት_አልሆንም

የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ አመራሮች፣ ቡድን መሪዎች፣ የጣቢያ ኃላፊዎች፣ የትራፊክ ፖሊሶች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት “ምክንያት አልሆንም” በሚል መሪ ቃል በዛሬው ዕለት በኢንተርፕራይዙ አዳራሽ ግምገማዊ ውይይት ተካሄዷል።

በውይይቱም በተቋም ደረጃ የኮሮና ቫይረስ በሽታን ለመከላከል የተከናወኑ ተግባራት ተነስተዋል። የኮሮና በሽታ መከላከል ግብረ ኃይል በማቋቋም፤ ሰፊ የግንዛቤ ማስፋፊያ ስራዎች በመስራት፤ አስፈላጊ ግብዓቶችን በማሟላት፤ የተቋሙን ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ፤ ክትትል እና ድጋፍ በማድረግ እንዲሁም የእርምት እርምጃዎች በመውሰድ በሽታው በተቋሙ ላይ ሊያደርስ ይችል የነበረውን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳት እንዲሁም የገጽታ ግንባታ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ትጽዕኖ በመከላከል ረገድ ተጠቃሽ ስራዎች ናችው።

ኮሮናን ከዚህ በበለጠ እንዳይስፋፋ ምክንያት ላለመሆን ኃላፊነትን መወጣት እንደሚገባ በመጠቆም፤ ቸልተኝነት እና መመሪያዎችን የማክበር ውስንነት የታዩ ክፍተቶች መሆናቸው ከተሳታፊዎች ተነስቷል።

የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ዋ/ስ/አስኪያጅ አቶ ሙስጠፋ አባሲመል የታዩ ክፍተቶችን ለማረም ክትትል እና ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ በማሳሰብ፤ “በእንቅስቃሴዎቻችን ሁሉ የኮሮና መከላከያ መንገዶችን በመተግበር ለበሽታው መስፋፋት ምክንያት መሆን የለብንም” በማለት ውይይቱን አጠቃለዋል።