ከባድ የዝርፊያ ወንጀል የፈፀሙ ተከሳሾች በእስራት ተቀጡ!

ከባድ የዝርፊያ ወንጀል የፈፀሙ ተከሳሾች በእስራት ተቀጡ!

የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ በሚያስተዳድረው የአዲስ አበባ- አዳማ የፍጥን መንገድ ላይ በተለያየ ጊዜ የጸጥታ ስጋቶች እና የስርቆት ወንጀሎች ሲፈፀሙና ክትትል ሲደረግባቸው እንደነበር በመጥቀስ የሚደርሱ ጥቆማዎችን መሰረት አድርጎ ከፍተኛ ስራዎች መሰራታቸውን ገልጿል፡፡
በዚህም ዘራፊዎችን ተከታትሎ ለመያዝ ከማህበረሰቡ ጋር የተደረጉ ውይይቶች፣ በመንገዱ ዙሪያ ካሉ የከተማ አስተዳደር የጸጥታ ዘርፎች ጋር የተሰሩ ስራዎች ያደረጉት አስተዋፅኦ እንዳለ ሆኖ በተለይ ተጠርጣሪዎችን ተከታትለው በቁጥጥር ስር ያዋሉት በአዳማ ከተማ የቦኩ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ጽ/ቤት ከኢንተርፕራይዙ ፀጥታ ዘርፍ ጋር በመቀናጀት ነው፡፡
የሚደርሱ ጥቆማዎችን መሰረት በማድረግም በተደረገ ክትትል 5 ተጠርጣሪዎችን፣ በፍጥነት መንገዱ ላይ እንዲሁም ከሌላ ቦታ የተሰረቁ አብዛኛውን ንብረቶች እና ለዝርፊያ የሚጠቀሙባቸውን ቁሳቁሶች በኤግዚቢትነት መያዝ መቻሉን የቦኩ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ጽ/ቤት ጠቅሷል፡፡
ተጠርጣሪዎቹን በመያዝ ወደ ማረፊያ ክፍል እንዲቆዩ በማድረግ ፖሊስ መረጃዎችን አደራጅቶ ለአቃቤ ህግ በማቅረብ ክስ የመሰረት ሲሆን ክሱ የቀረበለት የአዳማ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ግራ ቀኝ የቀረቡ ማስረጃዎች ላይ እንዲከራከሩ አድርጓል፡፡

ክርክሩን ያጤነው ፍርድ ቤትም በወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንቀፅ 671/1//ሐ/ ላይ የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ በከባድ ውንብድና ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው፤ ግለሰቦቹን ያርማል ህበረተሰቡን ያስተምራል በማለት፤ በ1ኛ ተከሳሽ አቶ አበባ ቶጱ፣ 2ኛ ተከሳሽ አቶ ጎሳ ግርማ እና 3ኛ ተከሳሽ በሆኑት አቶ ተሾመ ገመቹ ላይ በተጠረጠሩበት ከባድ የዝረፊያ ወንጀል በ16 ዓመት ከስድስት ወር እና 4ኛ ተከሳሽ አቶ ንጉሱ መገርሳ ላይ በ15 ዓመት እንዲሁም 5ኛ ተከሳሽ አቶ ካሳሁን ወይም ግርማ ስንታየሁ በመባል በሚጠሩት ተጠርጣሪ ላይ የ3 ወር ጽኑ እስራት በይኗል፡፡

ኢንተርፕራዙ በቀጣይም የመንገዱን ደህንነት ለማስጠበቅ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ግንኙነቱን በማጠናከር፤ የተለያዩ ስልቶችን በመንደፍ በርካታ ተግባራትን እንደሚከውን እያስታወሰ አሁን ለተገኘው ውጤት ህብረተሰቡ እና የፀጥታ አካላት ላደረጉት ርብርብ ምስጋናውን ያቀርባል፡፡

የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ

ደህንነትዎ የክብር ስማችን ነው!