የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ በ10/04/2013 ዓ.ም፣ በአዲስ አበባ ከተማ፣ ሀርመኒ ሆቴል “ኤክስፕረስ ማይልስ” አዋርድ (ExpressMiles Award) በሚል መጠሪያ ለደህንነት አምባሳደሮች ዕውቅና እና ሽልማት ሰጥቷል።
በዕለቱም የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር እና የኢንተርፕራይዙ የቦርድ አባል ዶ/ር ሹመቴ ግዛው፣ የተለያዩ ተቋማት ኃላፊዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተገኙ ሲሆን የዕውቅና ፕሮግራም መዘጋጀቱ የመንገድ ደህንነትን ከማረጋገጥ አኳያ አዎንታዊ አስተዋጽዖ እንዳለው ገልጸዋል።
የኢንተርፕራይዙ ዋ/ስ/አስኪያጅ አቶ ሙስጠፋ አባሲመል የዕውቅና እና የሽልማት ፕሮግራሙ በዋናነት የሚያጠፉ አሽከርካሪዎችን መውቀስ እና ተጠያቂ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ህግ እና ደንብ አክብረው የሚሰሩ አሽከርካሪዎችን የማመስገን ልምድ እንዲዳብር ለማድረግ እንዲሁም ሌሎች አሽከርካሪዎችን ለማነሳሳት ያለመ ነው፤ ብለዋል።
አሽከርካሪዎች ምንም አይነት አደጋ አለማድረሳቸው፤ በፍጥነት መንገዱ ብዙ ምልልስ ማድረጋቸው እንዲሁም በመልካም ስነ ምግባር ማሽከርከራቸው ለሽልማት እንዲበቁ ማድረጉ ተነግሯል። የደህንነት አምባሳደሮቹ ኢንተርፕራይዙ የሰጣቸው ዕውቅና እና ሽልማት እንዳስደሰታቸው በመግለጽ በቀጣይ በተሻለ መልኩ እንዲተጉ መነሳሳት እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል፡፡