የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ስራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ያልተቋረጠ የ24/7 አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ አገልግሎቱን ያለማቋረጥ የሚሰጠው ይህ ተቋም ቀልጣፋና ዘመናዊ በሆነ መልኩ የተጠቃሚዎቹን ፍላጎት ለማሟላት የተለያዩ ተግባራትን ሲከውን ቆይቷል፡፡ በተያዘው የ2013ዓ.ም በጀት ዓመት በአዲስ- አዳማ እና በድሬዳዋ- ደወሌ የክፍያ መንገዶች 8,925,529 የትራፊክ ፍሰት ለማስተናገድ ታቅዶ 8,856,001 በማስተናገድ ተችሏል፡፡ ፍሰቱም 99.22 % ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
በተጨማሪም ከክፍያ መንገድ አገልግሎት ብር 385,795,333 ለመሰብሰብ ታቅዶ 381,862,920 ብር ተሰብስቧል፡፡ እንዲሁም ከልዩ ልዩ ገቢዎች (ከማስታወቂያ ቦታዎች ኪራይ፣ ከወደሙ የመንገድ ሃብቶች ካሳ ክፍያ፣ ከተሽከርካሪ ማንሻና መጎተቻ…መሰል ክፍያዎች) ብር 25,892,237 ብር በማከል በአጠቃላይ ብር 401,004,247.65 ብር መሰብሰብ ተችሏል፡፡ ገቢውም 98.85% ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ገቢው ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ 8.4% ጭማሪ አሳይቷል፡፡
የመንገዱን ደህንነት ከማስጠበቅ አኳያ በተለያዩ ቦታዎች ሰፊ የግንዛቤ መፍጠሪያ መርሃ ግብሮችን በማዘጋጀት፤ በማስተማር እና አደጋ በሚያጋጥም ጊዜም የአደጋ መቆጣጠሪያ እና የጉዳት መቀነሻ መለኪያዎች መሰረት በማድረግ ፤ በደረሰ አደጋ የተዘጉ የመንገድ ክፍሎችን በፍጥነት ክፍት በማድረግ የትራፊክ ፍሰት እንዲቀጥል ማድረግ ተችሏል፡፡
በተጨማሪም የጥገና አቅምን በማሳደግ በውስጥ አቅም 6.2 ኪ.ሜ የመንገድ አካፋይ ብረት (Gardrail) እንዲሁም 1.35 ኪ.ሜ ርዝመት ያለው የአጥር ጥገና በአዲስ- አዳማ የፍጥነት መንገድ ላይ ተከናውኗል፡፡ እንዲሁም በአገልግሎት እድሜ ማብቃት እና በአደጋ ምክንያት በመንገድ ንብረቶች ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን በመጠገን የመንገዱ ምቾት እና ደህንነት እንዳይጓደል ተሰርቷል፡፡
በየጊዜው የሚያጋጥሙ የትራፊክ አደጋዎች ፤ለመንገዱ ጥገና የሚውሉ የመለዋወጫ ዕቃዎች እጥረት ፤በድረደዋ ደወሌ የክፍያ መንገድ ላይ የሚስተዋለው የወደብ እቃዎችን ከክብደት በላይ ጭኖ መንገዱን መጠቀም ዋነኛ ተግዳሮቶች ቢሆኑም አሁን አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙትን እንዲሁም በቀጣይ ግንባታቸው ተጠናቆ የሚረከባቸውን የክፍያ መንገዶች ለማስተዳደርና የአገልግሎት አሰጣጥ አቅሙን ለማሳደግ የተገኙ ተሞክሮዎችን በመቀመር፤ የታዩ ውስንነቶችን በጥልቀት በመገምገም እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የማስተካከያ እርምጃዎችን በመውሰድ፤ የነበሩ ጠንካራ ጎኖችን በማዳበርሃገራዊ ተልዕኮውን ለመፈጸም ይተጋል፡፡