በመንገድ ደህንነት እና ጸጥታ ዙሪያ ተከታታይ ውይይቶችን በማድረግ ወደ ተግባር መቀየር እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ በሞጆ- ባቱና አዲስ- አዳማ መንገድ ዙሪያ ካሉ የከተማ አስተዳደር፣ የጸጥታ አካላት፣ የመንገድ ደህንነት ባለሙያዎች፣ ትራፊክ ፖሊሶች ጋር በፍጥነት መንገድ ላይ የሚያጋጥሙ የጸጥታ ስጋቶችና የመንገድ ንብረት ስርቆቶችን ለማስቀረት የሚያስችል ውይይት ተካሄደ፡፡
በሞጆ ከተማ በተደረገው በዚህ ውይይት ላይ ባቱ፣ መቂ፣ ቆቃ፣ ቦቴ ሞጆ ከተሞች እንዲሁም የምስራቅ ሸዋ ፖሊስ አዛዥና የጸጥታ ዘርፍ ኃላፊዎች በተገኙበት መንገድ ላይ እያጋጠሙ ስላሉ የጉዞ ላይ ደህንነት ስጋቶች፣ የትራፊክ አደጋ መንስዔዎች እንዲሁም በመንገዱ ንብረት ላይ ስለሚያጋጥሙ ስርቆቶች ውይይት ተደርጓል፡፡
በዕለቱ በመድረኩ የተገኙት የኢንተርፕራይዙ የስራ ኃላፊዎች በችግሮቹ መንስዔዎችና በመፍትሔዎች ላይ ገንቢ ውይይት ከማድረጋቸው ባሻገር ሁሉንም ችግሮች ከመሰረቱ በመለየት መፍትሔ ለማዘጋጀት የሚያግዙ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠልና ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ በዕለቱ የተገኙ የፖሊስና የጸጥታ አካላት በበኩላቸው ለተቋሙ አገልግሎት ውጤታማነት ደህንነቱ የተጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት እንዲያስችል የተቋሙ የመንገድ ደህንነት ቡድን የኦሮሚያ ፖሊስ በጋራ ሊሰሩ ይገባል ብለዋል፡፡