በድሬደዋ ደወሌ የክፍያ መንገድ ላይ የሚስተዋሉ የመንገድ እና የጉዞ ደህንነት ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል ውይይት ተደረገ፡፡

የክፍያ እና የፍጥነት መንገዶች ላይ የሚከሰቱ የመንገድ እና የጉዞ ደህንነት ችግሮች አገልግሎቱን ከማስተጓጎል ባለፈ የተጠቃሚውን እርካታ እንደሚቀንሱ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ከሚያስተዳድራቸው መንንገዶች አንዱ በሆነዉ የድሬደዋ- ደወሌ መንገድ ላይ የሚስተዋሉ ከዚህ በፊት ያልነበሩና በክልሉ መንግስት እዉቅና ያልተሰጣቸዉ በትራንስፖርት ቁጥጥር፣ ትራፊክ ደህንነትና በመሳሳሉት ስራዎች ሽፋን የሚንቀሳቀሱ አካላት የክፍያ መንገዱን ተጠቃሚ ደንበኞችን  በተለያዩ ቦታዎች በማስቆም ህገ-ወጥ ክፍያ የሚሰበስቡ በመኖራቸው ከመንገዱ ተጠቃሚዎች ተደጋጋሚ ቅሬታዎች ሲቀርብ መቆየቱ ተገልጿል፡፡

በመሆኑም ይህ ተግባር ኢንተርፕራይዙ በአዋጅ የተሰጠውን ስልጣንና ሃላፊነት እንዳይወጣ ከማደናቀፉም በላይ ህገ-ወጥ በሆነ መንገድ ግለሰቦች የሚፈጽሙት ኃላፊነት የጎደለዉ ተግባር የክልሉን መንግስት መልካም ስም የሚያጎድግድፍ በመሆኑ በጋራ በመሆን በፍጥነት ማስቆም አሰፈላጊ በመሆኑ የክልሉ መንግስት እና የኢንተርፕራይዙ ከፍተኛ አመራሮች የጋራ ዉይይት ማገሄዳቸዉ ተገልጿል፡፡

የሶማሌ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ምክትል ፕሬዝደንትና የኢንተርፕራይዙ የቦርድ አባል ክቡር አቶ ኢብራሂም ኡስማን እንዲሁም ከክልሉ የፖሊስ አዛዥ ኮሚሽነር ሙሀመድ ሀሰን  ከኢንተርፕራይዙ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሙስጠፋ አባሲመል እንዲሁም የድሬደዋ ደወሌ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ሮብሌ አሊ በጋራ በመሆን ባካሄዱት ውጤታማ ውይይት ከስምምነት መደረስ መቻሉ ተገልጿል፡፡

በዚዉ መሰረትም በክልሉ እና በፌዴራል መንግስት እዉቅና ካላቸዉ በስተቀር የህገወጥ-የሰዎች ዝዉዉርና የኮንትሮባንድ ተግባር ላይ በተሰማሩ አካላት እንዳይጭበረበሩ በህጋዊ የገቢ ደረሰኝ በተፈቀዱ ኬላዎች ላይ ብቻ ከሚሰበሰብ ቀረጥ ዉጪ ማንኛዉም አካል በመንጉዱ ላይ ተሽከርካሪዎችን አስቁሞ ገንዘብ መቀበል ስለማይችል ድርጊቱን ማስቆም እንዲያስችል ተግባሩን የሚፈጽሙ ካሉ የሚቆጣጣርና በተጨማሪም የመንገዱ እና የመንገደኞች ደህንነት የሚያሰከብሩ 12 መደበኛ ፖሊስ 8 የትራፊክ ፖሊስ አባላትን በመመደብ ስራ መጀመር መቻሉ ተራጋግጧል፡፡

በመሆኑም ኢንተርፕራይዙ የክልሉ መንግስት ለችግሩ ክብደት በመስጠትና ለሳዩት ቁርጠኝነት የላቀ ምስጋናዉን እያቀረበ የመንገዱ ተጠቃሚ ደንበኞቹም ይህንኑ አዉቀው ያለ አግባብ በህገ-ወጥ መንገድ ለሚጠየቁትን ገንዘብ ክፍያ እንዳይፈፅሙ ችግሮቹ ሲያጋጥሙም  ለኢንተርፐራይዙ በ8808 ነጻ የስልክ መሰመር እና በ0258903797 መደበኛ ስልኮች ላይ በመደወል ጥቆማቸዉን አንዲያቀርቡ ተገልጿል፡፡