================================
ኢክመኢ [ETRE ጳጉሜ 03/2018 ዓ/ም]
የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ የ2018 ዓ.ም. የሥራ አፈጻጸሙን ገምግሞ የ2019 ዓ.ም. የሥራ ዕቅድና የትኩረት አቅጣጫዎችን ከሠራተኞች ጋር ተወያይቷል።
በአዲስ አበባ ግዮን ሆቴል በተካሄደው መድረክ፣ የኢንተርፕራይዙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሙስጠፋ አባሲመል በ2018 ዓ.ም የተመዘገበው ውጤት የአመራሩ፣ የሠራተኞችና የባለድርሻ አካላት የጋራ ጥረት ውጤት መሆኑን ገልጸው፣ ለተደረገው አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።
የዋና ሥራ አስፈጻሚ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አእምሮ መኩሪያ የ2018 ዓ.ም. የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቱን ሲያቀርቡ፣ ኢንተርፕራይዙ 12.81 ሚሊዮን ተሽከርካሪዎችን በማስተናገድ 2.5 ቢሊዮን ብር ገቢ እና ከታክስ በፊት 1.47 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማስመዝገቡን ገልጸዋል። ተቋሙም በ7 ስትራቴጂያዊ ግቦችና በ51 ቁልፍ የአፈጻጸም አመልካቾች (KPIs) መሠረት 94.49 በመቶ አጠቃላይ አፈጻጸም ማስመዝገቡ ተገልጿል።
በዓመቱ ከተመዘገቡ ዋና ዋና ስኬቶች መካከል፦ በአዲስ-አዳማ መስመር ኪ.ሜ. 29 ላይ የተገነባው ሁለገብ የአገልግሎት ማዕከል ለደንበኞች ክፍት መደረጉ፣ የዲጂታል ክፍያ አማራጮች ሥራ ላይ መዋላቸው፣ በሞጆ-ሐዋሳ መስመር ዘመናዊ የትራፊክ አስተዳደርና ቁጥጥር ሥርዓት (ITS) ተግባራዊ መሆኑ እንዲሁም ISO 9001 እና ISO 45001 የዓለም አቀፍ ሰርቲፊኬቶችን ማግኘቱ ተጠቃሽ ናቸው።
በመድረኩ ሠራተኞች በ2018 ዓ.ም. አፈጻጸምና በ2019 ዓ.ም. ዕቅድ ዙሪያ ጥያቄዎችና የማሻሻያ ሃሳቦችን አቅርበዋል። በተለይም የዲጂታል አገልግሎት ማስፋፋት፣ የደንበኛ እርካታን ማሳደግ፣ የሠራተኞችን አቅም ማጎልበትና የገቢ ምንጮችን ማጠናከር ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጓል።
የቀረቡት ጥያቄዎችና ሃሳቦች የ2019 ዓ.ም የሥራ ዕቅድ ትግበራ ላይ ታሳቢ እንደሚደረጉ ተገልጾ፣ የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት የሁሉም ሠራተኞችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑ ተጠቁሟል።
ከመድረኩ በኋላ የኢንተርፕራይዙ ሠራተኞች በታደሰውና ለሕዝብ ክፍት በሆነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ-መንግሥት ጉብኝት በማድረግ የሀገሪቱን ታሪክ፣ ቅርስና ባህላዊ እሴቶች ተመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ
ደህንነትዎ የክብር ስማችን ነው!

