================================
ኢክመኢ [ETRE ሐምሌ 12/2018 ዓ/ም]
በኢትዮጵያ የሰራተኞች ማህበራት ኮንፌዴረሽን (ኢ/ሰ/ማ/ኮ) አዘጋጅነት ሲካሄድ የነበረው የ2018 በጀት ዓመት የሰራተኞች የበጋ ወራት ስፖርት ውድድር በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም በደማቅ ሥነ-ሥርዓት ተጠናቀቀ።
የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች በመሳተፍ ከፍተኛ ብቃት ያሳየ ሲሆን፣ በውድድሩ ማጠቃለያ ላይ አስደናቂ ውጤት ማስመዝገብ ችሏል። ኢንተርፕራይዙ በሴቶች የገመድ ጉተታ ውድድር አጠቃላይ አሸናፊ በመሆን የዋንጫ እና የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኗል። እንዲሁም በወንዶች የገመድ ጉተታ ውድድር የብር ሜዳሊያ በማግኘት ለተቋሙ ክብር አምጥተዋል። በተጨማሪም በውድድሩ ላይ ላሳዩት ንቁ ተሳትፎ ሰርተፊኬት ተበርክቶላቸዋል።
ኢንተርፕራይዙ በእግር ኳስ፣ በመረብ ኳስ፣ በዳርት፣ በጠረቤዛ ቴኒስ፣ በገመድ ጉተታ እና በዳማ (ቼዝ) ተወዳዳሪዎቹን በማሳተፍ በውድድሩ የነበረውን ቆይታ በስኬት አጠናቋል። ይህ የስፖርት ውድድር የሰራተኞችን የአካል ብቃት ከማጎልበት ባሻገር፣ የቡድን መንፈስን፣ የተቋሙን ውስጣዊ አንድነት እና የማህበራዊ ግንኙነትን ለማጠናከር ከፍተኛ ሚና እንደነበረው ተገልጿል።
በውድድሩ መዝጊያ ሥነ-ሥርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት የኢ/ሰ/ማ/ኮ ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ካሳሁን ፎሌ፣ ተቋማት ለሰራተኞቻቸው አንድነት እንዲህ ዓይነት ውድድሮች ያላቸውን ፋይዳ አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል። አያይዘውም ተወዳዳሪዎች በውድድሩ ወቅት ላሳዩት መልካም ስነ-ምግባር እና የቡድን መንፈስ አድናቆታቸውን በመግለጽ፣ ይህንን ተሞክሮ በቀጣይም አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች ያስመዘገበው ድል፣ ለስፖርት ተሳትፎ ብቻ ሳይሆን ለጤናማ የህይወት መንገድ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው። ኢንተርፕራይዙ በቀጣይ ጊዜያትም በሌሎች ዘርፎች ውጤታማ እና ምሳሌ የሚሆን አፈጻጸም ለማሳየት ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።
የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ
ደህንነትዎ የክብር ስማችን ነው!!

