================================
ኢክመኢ [ETRE ሐምሌ 18/2018 ዓ.ም]
አብዛኛዎቹ የቦርዱ አባላት በቅርቡ በአዲስ መልክ የተመደቡ በመሆናቸው ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ተመድበው የመጡት ከፍተኛ ባለሙያዎች በቦርድ አስተዳደር መመሪያ ላይ አጭር ስልጠና ለቦርዱ አባላት የሰጡ ሲሆን፣ በመቀጠልም የቦርዱ ሰብሳቢ የተከበሩ ክቡር ዶ/ር ተሾመ አዱኛ ለዕለቱ የተያዘውን አጀንዳ በማስጸደቅ መደበኛ ስብሰባውን አስጀምረዋል ።
በዚህ መሠረትም በኢንተርፕራይዙ አመራሮች ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ ባለፉት 12 ዓመታት ያከናወናቸው ዋና ዋና የልማት እንቅስቃሴዎች፣ ያስመዘገባቸው አፈጻጸሞች፣ የተቋሙ ታሪካዊ የእድገት ጉዞ እንዲሁም በቀጣይ ትኩረት የሚሹ አቅጣጫዎችን የሚዳስስ ሰፊ ገለጻ ቀርቧል። ይህም ለአዲሱ ቦርድ ስለ ተቋሙ አጠቃላይ እንቅስቃሴ ተረድቶ እንዲመራ ግንዛቤ መፍጠር አስችሏል።
የኢንተርፕራይዙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሙስጠፋ አባሲመል የ2018 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን፣ ተቋሙ በበጀት ዓመቱ ከፍተኛ ውጤቶችን ማስመዝገቡን ገልጸዋል። በበጀት ዓመቱ የተቀመጡትን ሁሉንም ተግባራት መሠረት በማድረግ የተቋሙ አጠቃላይ የሥራ አፈጻጸም 94.49% መሆኑ ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ አወንታዊ አፈጻጸም ከታየባቸው ዋና ዋና መስኮች መካከል የኤሌክትሮኒክስ የክፍያ አሰባሰብ ሥርዓት “TOLO” በተሳካ ሁኔታ ሥራ ላይ መዋሉ እና በአዲስ-አዳማ ኪ.ሜ 29 ላይ የተገነባ የአገልግሎት መስጫ ሥራ መጀመሩ፣እንዲሁም ተቋሙ ከፍተኛ ትርፍ ያስመዘገበ መሆኑ በጠንካራ ጎን ከተነሱት ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ፤ የዘመናዊ የትራፊክ አስተዳደር ሥርዓት (ITS – Intelligent Transport System) ትግበራ በሙሉ አቅሙ ወደ ትግበራ አለመገባቱ እና አዳዲስ አማራጭ የገቢ ምንጮችን መፍጠር አለመቻል በክፍተት የተለዩና በቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መሆናቸው ተመልክቷ።
የዳይሬክተሮች ቦርዱ የቀረበውን የ2018 በጀት ዓመት አጠቃላይ የሥራ አፈጻጸም ከመረመረ በኋላ የቀረበውን የ2019 በጀት ዓመት የሥራ ዕቅድ በጥልቀት ተወያይቶ ሙሉ በሙሉ አጽድቋል።
በስብሰባው ማጠቃለያ ላይ የኢንተርፕራይዙ የቦርድ ሰብሳቢ ባስተላለፉት መልእክት፣ በተጠናቀቀው የ2018 በጀት ዓመት የታቀዱ ግቦችና የተመዘገቡ ስኬቶች ዳር እንዲደርሱ ላበረከቱት የጎላ አስተዋጽዖ ለተቋሙ አመራሮችና ሰራተኞች፣ ለደንበኞች እንዲሁም ለባለድርሻ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበው፣ ለ2019 በጀት ዓመት የተቀመጡትን ስልታዊ ግቦች ለማሳካት ከፍተኛ ጥረትና ቁርጠኝነት የሚጠይቅ በመሆኑ፣ የሥራ አመራሩና መላው የኢንተርፕራይዙ ሰራተኞች የተጣለባቸውን ኃላፊነት በብቃት እንዲወጡ በማሳሰብ ስብሰባው ተጠናቋል።
የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ
ደህንነትዎ የክብር ስማችን ነው!!

